የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደማስቆ ሲገቡ የጥይት መከላከያ ለብሰዋል
ሚኒስትሯ ከአሳድ መወገድ በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው እያደረጉ የሚገኙት ከፈረንሳይ አቻቸው ጋር ነው
ሚኒስትሮቹ በሶሪያ ዘላቂ መረጋጋት በሚያመጡ ጉዳዮች ዙሪያ ከአህመድ አል ሻራ ጋር ይወያያሉ ተብሏል
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርኮክ ለይፋዊ ጉብኝት ሶሪያ ገብተዋል።
ከአሳድ መወገድ በኋላ በሶሪያ የመጀመሪያ ጉብኝትታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ቤርኮክ ደማስቆ ሲገቡ የጥይት መከላከያ መልበሳቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
ሚኒስትሯ ከወታደራዊ አውሮፕላን እንደወረዱ የጥይት መከላከያ መልበሳቸውን የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂን ኖል ባሮትም ከጀርመን አቻቸው ጋር ደማስቆ መግባታቸውን አናዶሉ ዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በሶሪያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በሚካሄድበትና ዘላቂ መረጋጋትን ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከሶሪያ ጊዜያዊ መሪ አህመድ አል ሻራ ጋር እንደሚመክሩ ነው የተነገረው።
ሚኒስትሮቹ ከአል ሻራ ጋር ሲመክሩ የአውሮፓ ሀገራትን በመወከል ጭምር መሆኑን የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መገለጫ ጠቁሟል።
የበሽር አል አሳድ የ24 አመታት አገዛዝን የጣለው ቡድን ጊዜያዊ መንግስት አዋቅሮ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ጀምሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አሳድ አል ሺባኒ በሳኡዲ አረቢያ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
የዩክሬንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች (በጥይት መከላከያ)ም ቢሆን ደማስቆ በመግባት ከአህመድ አል ሻራ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር ምክክር እያደረጉ ነው።
በውይይቶቹ በአሳድ የአግዛዝ ዘመን በሶሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ተነስተው ሀገራት የደማስቆም የመልሶ ግንባታ እንዲያግዙ ጥሪ እያቀረቡ ስለመሆኑም ተዘግቧል።
በመጋቢት 2025 ስልጣናቸው ያበቃል የተባለላቸው አህመድ አል ሻራ ምርጫ ለማካሄድ በጥቂቱ አራት አመት ያስፈልጋል ማለታቸውና በገና በዓል ሰሞን የታዩት ግጭቶች ሶሪያውንን ስጋት ውስጥ ጥለዋል።
እስራኤል በሶሪያ የምትፈጽመው ድብደባ መቀጠልና የድንበር አካባቢ ሁኔታ የፈራረሰችውን ሀገር ለሌላ ዙር ጦርነት እንዳይዳርግ ስጋት ፈጥሯል።