ታንኮቹን መላክ በቀጥታ የጦርነቱ ተሳታፊ ያደርገኛል በሚል ስታቅማማ የቆየችው በርሊን በምዕራባውያን ጫና በጥር ወር አቋሟን መለወጧ ይታወሳል
የጀርመን ሊዮፓርድ 2 ታንኮች ዩክሬን መድረሳቸውን የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ።
በርሊን 18 ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን ነው ወደ ኬቭ የላከችው።
“ታንኮቹ በእርግጠኝነት በጦርነቱ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል” ብለዋል የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትሩ ቦሪስ ፒስቶሪየስ።
ከታንኮቹ ባሻገር 40 ጀርመን ሰራሽ “ማርደር” ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችም ኬቭ መድረሳቸው ተገልጿል።
ጀርመን ታንኮቹን እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎቹን የሚያሽከረክሩ ዩክሬናውያን ባለሙያዎችን ለሳምንታት ማሰልጠኗ የሚታወስ ነው።
ኬቭ የበርሊንን ድጋፍ ሩሲያን በአውደ ውጊያዎች ለመርታት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራቸው ገልጻለች ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ሞስኮ ግን “ግልጽ ጸብ አጫሪነት ነው” በሚል ተቃውሞዋን ማሰማቷ ነው የተዘገበው።
ጀርመን ምዕራባውያን ካሏቸው ታንኮች የሚስተካከለው የለም የሚባልለትን ሊዮፓርድ 2 ወደ ዩክሬን እንድትልክ ለቀረበላት ጥያቄ “በጦርነቱ እጄን በቀጥታ እንዳስገባ ያደርገኛል” በሚል ሳትቀበለው ቆይታለች።
ይሁን እንጂ ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ በኩል ከፍተኛ ጫና ተደርጎባት ባለፈው ጥር ወር ታንኮቹን ለመላክ መስማማቷ የሚታወስ ነው።
በርሊን ከዚህ ውሳኔ ላይ መድረሷን ተከትሎም ሊዮፓርድ 2 ታንክ ያላቸው ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም “ማርሽ ቀያሪ” ነው የሚባልለትን ታንክ ለመላክ መስማማታቸውም አይዘነጋም።
በትናንትናው እለትም ከጀርመን በተጨማሪ የፖርቹጋል ሊዮፓርድ 2 ታንኮች (ሁለት) ኬቭ መድረሳቸው ተገልጿል።