ጀርመን ለዩክሬን ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን ለመላክ ተስማማች
ታንኮቹን ወደ ኬቭ መላክ በራሴ ላይ ጦርነት ላይ እንደማወጅ ነው ስትል የቆየችው በርሊን የምዕራባውያኑን ጫና መቋቋም አልቻለችም
ሩሲያ የጀርመንን ውሳኔ እጅግ አደገኛ ነው ብላለች
ጀርመን ወደ ዩክሬን ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን ለመላክ መስማማቷን ዛሬ ይፋ አድርጋለች።
የመራሂ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ አስተዳደር ታንኮቹን ወደ ኬቭ እንዲልክ ባለፉት ሳምንታት ከፍተኛ ጫና ተደርጎበታል።
ጀርመን ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን ወደ ዩክሬን መላክ “ጦርነቱን ያባብሰዋል፤ በርሊንንም በቀጥታ ወደ ጦርነቱ ያስገባታል” በሚል ጉዳዩን ስታጤን ቆይታለች።
በዛሬው እለት ግን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባደረጉት ንግግር፥ ታንኮቹን ወደ ዩክሬን ለመላክ መወሰናቸውን ተናግረዋል።
“ጀርመን ለዩክሬን ድጋፍ ለማድረግ ሁሌም ከፊት ትሰለፋለች፤ ጦርነቱ በአውሮፓ ከበርሊን በቅርብ ርቀት በዩክሬን እንደመካሄዱ ድጋፍ ማድረጋችን ተገቢ ነው” ሲሉም ነው የተደመጡት።
በርሊን ለኬቭ ድጋፍ ለማድረግ ወደኋላ የማትል ቢሆንም ጦርነቱ እንዲባባስ ግን ፍላጎት እንደሌላትም አብራርተዋል።
የሊዮፓርድ 2 ታንኮቹ መላክ የጀርመንን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል አለመሆኑንም ዜጎቻቸው እንዲረዱ ነው የጠየቁት።
ጀርመን ከራሷ ክምችት 14 ታንኮችን ለዩክሬን ለመስጠት የወሰነች ሲሆን፥ በሶስት ወይም በአራት ወራት ውስጥ ኬቭ መሳሪያዎቹ እንደሚደርሷት ተነግሯል።
የዩክሬን ወታደሮችን የማሰልጠኑ እና የታንክ መሳሪያዎችን የማቅረቡም ስራ በፍጥነት ይከናወናል ነው ያሉት የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ።
የበርሊን ውሳኔ እንደ ፖላንድ፣ ስፔን፣ ፊንላንድ እና ኔዘርላንድስ ያሉ ሀገራት ያሏቸውን ሊዮፓርድ 2 ታንኮች ወደ ኬቭ እንዲልኩ ያስችላቸዋል ተብሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የሾልዝ አስተዳደር ያሳለፈውን ውሳኔ “በጣም ወሳኝ እና ጊዜውን የጠበቀ” ብለውታል።
ሌሎች ጀርመን ሰራሹን ታንክ የታጠቁ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንደገቡላቸውም በማከል።
ሩስያ በበኩሏ የበርሊንን ውሳኔ የምዕራባውያን ጦርነቱን የማስቀጠል ፍላጎት ማሳያ አድርጋ አቅርባዋለች።
በበርሊን የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ፥ “ውሳኔው እጅግ አደገኛ ነው” ብሏል።
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ናዚዎች ከፈጸሙት ወንጀል ጋርም ለማገናኘት ሞክሯል።
ብሪታንያ፣ ፖላንድ፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ግን የኦላፍ ሾልዝን ውሳኔ በአዎንታ ተቀብለውታል።
ዋሽንግተን እና ፓሪስ ታንኮቻቸውን ወደ ኬቭ መላክ ስለማሰባቸው ግን ያሉት ነገር የለም።
የሩሲያ የጸጥታ ምክርቤት ምክትል ሊቀመንበሩ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ምዕራባውያን ለኬቭ የሚያደርጉት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ወደ ኒዩክሌር ጦርነት እንዳያስገባን ሲሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።