ጀርመን የውጭ ሀገራት ሰራተኞች በቀላሉ ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ የሚያስችለውን ደንብ አፀደቀች
አዲሱ ደንብ ጀርመንኛና እንግሊዝኛ ቋንቋ እስከቻሉ የውጭ ሀገራት ዜጎች ጀርመን ውስጥ እንዲሰሩ የሚፈቅድ ነው

ዛሬ የፀደቀው ደንብ በጤና፣ ግንባታና ቴክኖሎጂን በመሳሰሉ መስኮች የውጭ ዜጎች ጀርመን ገብተው እንዲሰሩ የሚያስችል ነው
ጀርመን የውጭ ሀገራት ሰራተኞች በቀላሉ ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ የሚያችለውን ደንብ አፀደቀች።
የጀርመን ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው ስብሰባው በተለያዩ ሙያ የሰለጠኑ ከአውሮፓ ህብረት ሀገራት ውጭ የሆኑ ሰራተኞች ወደ ጀርመን እንዲገቡ የሚፈቅደውን አዲስ ደንብ አድቋል።
እንደ ዶቸቬለ ዘገባ ከሆነ አዲሱ ደንብ ባለሙያዎች፣ የጀርመንኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋ እስከቻሉ ድረስ ቀበላሉ ወደ ጀርመን እንዲገቡና ጀርመን ውስጥ እንዲሰሩ የሚፈቅድ ነዉ።
በካናዳ ደንብና አሰራር መሠረት የተቀረፀ እንደሆነ የሚነገረዉ ደንብ በተለይ እንደ መስተንግዶ፣ ጤና፣ ግንባታና ቴክኖሎጂን በመሳሰሉ መስኮች ጀርመን ያለባትን የባለሙያ እጥረት ለማቃለል ይረዳል ተብሏል።
ጀርመን በየትኞቹ ዘርፎች ነው 2 ሚሊየን ሰራተኞችን እፈልጋለሁ ያለችው?
የጀርመንኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋ መቻል፣ የስራ ልምድ፣ ከጀርመን ጋር ያለ ነባር ግንኙነት እና እድሜ ዋነኛ መመልመያ መስፈርቶች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የጀርመን ሰራተኞች ሚኒስትር ሁበርተስ ሄይል ከመመለመያ መስፈርቶቹ ውስጥ ሶስቱን ያሟላ ወደ ጀርመን እንዲገባ ሊፈቀድ እንደሚችል ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወሳል።
አሁን ላይ ጀርመን የክህሎት ወይም ተግባር ሙያ ስራ ዘርፎች፣ የማህበረሰብ እንክብካቤ፣ የአረጋዊያን ጤና እና ትምህርት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ የሰራተኞች እጥረት ገጥሟታልም ተብሏል፡፡
የብረት እና ኤሌክትሪካል ሙያ ዘርፎችም ከፍተኛ የሰራተኛ እጥረት የገጠማቸው ዘርፎች ሲሆኑ የሰው ሀይል እጥረቱ በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ችግሩን መፍታት እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
ወጣት ጀርመናዊያን ቅንጡ የስራ ከባቢ መፈለግ፣ የሙያ ስራ ዘርፎች ላይ የመሰማራት ፍላጎት ማጣት እና ከፍተኛ ክፍያ መጠየቅ ለጀርመን ኢንዱስትሪዎች ዋነኛ ፈተና መሆኑንም ነው የተገለፀው።