ጀርመን በየትኞቹ ዘርፎች ነው 2 ሚሊየን ሰራተኞችን እፈልጋለሁ ያለችው?
ጀርመናዊያን ወጣቶች ቅንጡ የስራ ከባቢ መፈለግ እና ከፍተኛ ክፍያ መጠየቃቸው የሰራተኛ እጥረቱን አባብሶታል ተብሏል
በርሊን የገጠማትን የሰራተኞች እጥረት ለመፍታት የስደተኞች ፖሊሲዋን በመከለስ ላይ መሆኗን ገልጻለች
ጀርመን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰራተኞችን እንደምትፈልግ ገለጸች፡፡
የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቷ ጀርመን የሰለጠኙ ሰራተኞችን እንደምትፈልግ ያስታወቀች ሲሆን እጥረቱን ለመፍታት የስደተኞችን ፖሊስ እስከ ማሻሻል እንደምትደርስ አስታውቃለች፡፡
የሚሻሻለው የስደተኞች ፖሊሲም ሀገሪቱ የገጠማትን የሰራተኞች እጥረት በአጭር ጊዜ መፍታት እንደሚያስችላት የጀርመን የሰራተኞች እና የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር አስታውቋል፡፡
እንደ ዶቸቬለ ዘገባ ከሆነ ለዚህ የሚረዳ ረቂቅ ህግ ተዘጋጅቶ ለሀገሪቱ ካቢኔ የቀረበ ሲሆን ህጉ እንዲጸድቅ ለሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት ተልኳል፡፡
በዚህ ረቂቅ ህግ መሰረት ጀርመን ከአውሮፓ ውጪ ካሉ ሀገራት በዓት 60 ሺህ ሰራተኞችን ወደ ሀገሯ ለማስገባት ያስችላታል ተብሏል፡፡
ጀርመንኛ የስራ ቋንቋ መቻል፣ የስራ ልምድ፣ ከጀርመን ጋር ያለ ነባር ግንኙነት እና እድሜ ዋነኛ መመልመያ መስፈርቶች እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የጀርመን ሰራተኞች ሚኒስትር ሁበርተስ ሄይል ከመመለመያ መስፈርቶቹ ውስጥ ሶስቱን ያሟላ ወደ ጀርመን እንዲገባ ሊፈቀድ እንደሚችል መናገራቸው ተገልጿል፡፡
ወጣት ጀርመናዊያን ቅንጡ የስራ ከባቢ መፈለግ፣ የሙያ ስራ ዘርፎች ላይ የመሰማራት ፍላጎት ማጣት እና ከፍተኛ ክፍያ መጠየቅ ለጀርመን ኢንዱስትሪዎች ዋነኛ ፈተና መሆኑንም ነው ኒስትሩ የገለጹት።
አሁን ላይ ጀርመን የክህሎት ወይም ተግባር ሙያ ስራ ዘርፎች፣ የማህበረሰብ እንክብካቤ፣ የአረጋዊያን ጤና እና ትምህርት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ የሰራተኞች እጥረት ገጥሟታልም ተብሏል፡፡
የብረት እና ኤሌክትሪካል ሙያ ዘርፎችም ከፍተኛ የሰራተኛ እጥረት የገጠማቸው ዘርፎች ሲሆኑ የሰው ሀይል እጥረቱ በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ችግሩን መፍታት እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡