ጀርመንና ፈረንሳይ የሰላም ስምምነቱ አተገባበር የሚበረታታ መሆኑን ገለጹ
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከፈረንሳይና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ጠይቀዋል
በፌዴራል እና በህወሓት ባለስልጣናት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት አተገባበር የሚበረታታ መሆኑ የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ገልጸዋል።
የሰላም ስምምነቱን ለመደገፍ ኢትዮጵያ የሚገኙት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ተገናኝተው መምከራቸው ተሰምቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሁለቱ አውሮፓውያን ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ጋር “ጥልቅ እና ፍሬያማ” ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤርቦክ የጉብኝታቸው ዋና ዓላማ “ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላምና ለሰብዓዊ መብት ረገጣ ተጠያቂነት ለማስፈን” በምታደርገው ጉዞ ለመደገፍ ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና በበኩላቸው አውሮፓ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ለመቀጠል የተደረሰውን ስምምነት መተግበር እና ተጠያቂነትን ማስፈን ቅድመ ሁኔታ መሆኑን መናገራቸውን ኤፒ ዘግቧል።
በሰሜኑ ጦርነት ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አሳስበዋል።
በሁለት አመቱ ጦርነት የሆነው ሁሉ አሳዣኝ መሆኑ የገለጹት የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባርቦክ “ያለፍትህ ዘላቂ ሰላም የለም” ብለዋል።
“ሴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደመሆኔ አስገድዶ መድፈር የጦርነት አካል መሆኑ የተለመደ አይደለም። በጦርነት ወቅት ሰላማዊ ሰዎችን መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ዓለም አቀፉ የስብዓዊ መብት ሕግ በግልጽ ያስቀምጣል። አስገድዶ መድፈር የጦር ወንጀል ነው” ሲሉም ተናግረዋል ሚኒስትሯ።
ሚኒስትሮቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ወደሚገኘውና ከዩክሬን የተላከ ርዳታ የተከማቸበት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ማከማቻ መጋዘን የሚጎበኙ ይሆናል።
በጣም አስፈላጊ የሆነውን እህል ለማድረስ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቁት የሁለቱም ሀገራት መንግስታት በሰሜን ኢዮጵያ ጦርነት በጣም በተጎዱ አካባቢዎች ላሉ ሰዎች አዲስ ርዳታ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ሁለቱም አካላት ወደ ጠርጴዛ እንደመጡ ትልቁን ድርሻ ከተጫወተው የአፍሪካ ህብርት ባለስልጣናት ጋር ይገናኛሉም ተብሏል።