የብሪታንያ ንጉስ ቻርልስ ሀገራቸው በቅኝ ግዛት ዘመን በኬንያ ላይ ለሰራችው በደል ይቅርታ አልጠይቅም ማለታቸው ይታወሳል
ጀርመን በቅኝ ግዛት ዘመን በታንዛኒያ ላይ ለሰራችው በደል ይቅርታ ጠየቀች፡፡
የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቷ ጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴንሜር ታንዛኒያን እየጎበኙ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት የጀርመን ወታደሮች በታንዛኒያ ላይ የፈጸሙትን ግፍ አምነዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ የአሁኑ የጀርመን ትውልድ አባቶቻቸው እና አያቶቻቸው በአፍሪካ ግፍ መፈጸማቸውን ማወቅ አለባቸው ብለዋል፡፡
ጀርመን የአንደኛው የዓለም ጦርነት ከመከሰቱ በፊት በምስራቅ፣ ደቡብ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሀገራትን በቅኝ ግዛትነት ይዘው ቆይተዋል፡፡
የጀርመን ወታደሮች በተለይም በናሚቢያ እና ታንዛኒያ ሀገራቸውን ከቅኝ ግዛት ለማስለቀቅ የሚታገሉ ዜጎችን እያሳደዱ ይገድሉ እና ያሰቃዩ እንደነበር ፕሬዝዳንት ስቴንሜር በዳሬሰላም በነበራቸው ጉብኝት ወቅት ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት “የጀርመን ቅኝ ግዛት ወታደሮች በሰሩት በደል እኔ አፍራለሁ” ሲሉ ጠቅሰዋል ተብሏል፡፡
ማጂ ማጂ የተሰኘው የታንዛኒያ ነጻነት ታጋይ ስብስብ አባላት በጀርመን ወታደሮች የተጨፈጨፉ ሲሆን በአጠቃላይ ጀርመን 200 ሺህ ታንዛኒያዊያንን እንደገደለች ማመኗን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
አውሮፖ በቅኝ ግዛት ዘመን ለፈጸሙት በደል ይቅርታ ብቻውን በቂ ነው?
ጀርመን በናሚቢያ በተመሳሳይ በፈጸመችው በደል የዘር ማጥፋት መፈጸሙን ከሁለት ዓመቴ በፊት ማመኗ ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑ ናይሮቢ የነበሩት የብሪታንያ ንጉስ ቻርልስ ሀገራቸው በኬንያዊያን ላይ ለፈጸመችው በደል እንደሚጸጸቱ ገልጸው ይቅርታ ግን መጠየቅ እንደማይፈልጉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
አፍሪካን በቅኝ ግዛትነት ሲያስተዳድሩ የነበሩ ሀገራት መሪዎች ወደ አፍሪካ በመምጣት ለፈጸሟቸው የቅኝ ግዛት በደሎች ይቅርታ በመጠየቅ ላይ ሲሆኑ ቤልጂየም ከዚህ በፊት የኮንጎ ህዝቦችን ይቅርታ መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡