በጀርመን ጥምር መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ንግግር መካሄድ ጀመረ
በምርጫው የመሀል ግራ ዘመሙ የሶሻል ዴሞክራትስ ፓርቲ በጠባብ ውጤት ማሸነፉ ተንገሯል
የጥምር መንግስት ምስረታው ወራትን ይፈጃል የተባለ ሲሆን፤ እስከዚያው አንጌላ ሜርክል በኃላፊነታቸው ይቀጥላሉ
የጀርመን ቡንደስታግ ተብሎ የሚጠራው የሀገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት አባላት ምርጫ ባሳለፍነው እሁድ መካሄዱ ይታወቃል።
ትናንት ይፋ በተደረገው ጊዜያዊ ውጤት መሠረት የመሀል ግራ ዘመሙ የሶሻል ዴሞክራትስ ፓርቲ በጠባብ ውጤት ማሸነፉ ተነግሯል።
በጥቂት ድምጽ ብልጫ ያሸነፈው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ መንግስት ለመመስረት ተጣማሪ ፓርቲን ማግኘት እንደሚኖርበት የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።
ይህንን ተከትሎም የጀርመን ጥምር መንግስት የመመስረት ሂደት መጀመሩ የተነገረ ሲሆን፤ አወዛጋቢው ጥምር መንግስት የመመስረት ሂደት ወራት ያክል ጊዜ ሊወስድ ይችላል ተብሏል።
በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኘው ሶሻል ዴሞክራትስ ፓርቲ መሪ ኦላፍ ሾልዝ ከግሪን ወይም አረንጓዴ ፓርቲ እና ከሊብራሎች ጋር መስራት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።
ሆኖም ግን ክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረቱ አርሚን ላሼት በቀላሉ እጅ የሚሰጡ አይደልም እየተባለ ነው ያለው።
የጥምር መንግስት ምስረታው ወራትን ይፈጃል የተባለ ሲሆን፤ እስከዚያው ድረስ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በኃላፊነታቸው ይቀጥላሉ ተብሏል።
የጀርመን ቡንደስታግ ተብሎ የሚጠራው የሀገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት አባላት ምርጫ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በምርጫ ከሰጡ ድምጾች 25 ነጥብ 7 በመቶ እንዳገኘ መገለጹ ይታወሳል።
የመራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ የሆነው የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት እና የክርቲያን ሶሻል ኅብረት ጥምረት 24 ነጥብ 1 በመቶ ድምጽ አግኝቷል።
በምርጫው ግሪን ወይም አረንጓዴ ፓርቲ 14 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም ነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ 11 ነጥብ 5 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ጊዜዊ ውጤቱ ያመለክታል።