ጀርመን ሶስት ወር እና ከዛ በላይ የሆነው ጽንስ የተቋረጠባቸው ነፍሰጡሮች የወሊድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው የሚፈቅድ ህግ አዘጋጀች
በጀርመን በዓመት 84 ሺህ እርግዝናዎች እስከ ሶስት ወር ባሉት ጊዜ ውስጥ ይቋረጣሉ
አዲሱ ህግ ነፍሰጡሮች ተገቢ የህክምና እና ስነ ልቦና ድጋፍ አግኝተው ወደ ስራ እንዲመለሱ የሚፈቅድ ነው ተብሏል
ጀርመን ሶስት ወር እና ከዛ በላይ የሆነው ጽንስ የተቋረጠባቸው ነፍሰጡሮች የወሊድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው የሚፈቅድ ህግ አዘጋጀች።
የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን እናቶችን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ ህግ አውጥታለች።
አዲሱ ህግ በተለይም የጽንስ መቋረጥ የሚያጋጥማቸውን እናቶች ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
እንደ ዶቸ ቪሌ ዘገባ ከሆኑ አዲሱ ህግ ከሶስት ወራት ጊዜ ጀምሮ የጽንስ መቋረጥ ያጋጠማቸው ነፍሰ ጡሮች የወሊድ ፈቃድ እንዲያገኙ ይፈቅዳል።
በረቂቅ ደረጃ ያለው ይህ ህግ በአብዛኛው የምህር ቤት አባላት ይሁንታን አግኝቶ ወደ ሚቀጥለው ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
አዲሱ ህግ ከሶስት ወር ጀምሮ ጽንስ የተቋረጠባቸው እናቶች አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የበለጠ እድል ይሰጣል ተብሏል።
በስራ ያለው የጀርመን ህግ መሰረት የወሊድ ፈቃድ እንዲሰጥ የሚፈቅደው ለውልደት ስድስት ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ እንደሆነ ይደነግጋል።
እንዲሁም ከውልደት በኋላ ደግሞ ለስምንት ሳምንታት የወሊድ ፈቃድ እንዲሰጣቸውም ይፈቅዳል።
ይሁንና ጽንስ በተለያዩ ምክንያቶች ስለተቋረጠባቸው ነፍሰ ጡሮች ፈቃድ ስለሚያገኙበት ሁኔታ የሚፈቅድ አሰራር አልነበረውም ተብሏል።
በተለይም 24 ሳምንት እና ከዛ በላይ የሆነው ጽንስ ቢቋረጥ በወሊድ ፈቃድ እንዳይስተናገዱ ይከለክልም ነበር።
በዚህም መሰረት ከሶስት ወር ጀምሮ ጽንስ የተቋረጠባቸው ነፍሰጡሮች የወሊድ ፈቃድ እንዲያገኙ የሚፈቅድ ህግ ተዘጋጅቷል።
ረቂቅ ህጉ የፊታችን የካቲት ሰባት የመጨረሻ ውይይት ተደርጎበት ሊጸድቅ እንደሚችልም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
በጀርመን በየዓመቱ ከ84 ሺህ በላይ እርግዝናዎች ጸንሱ 12 ሳምንት ሳይሞላው ይጨናገፋል።