ቻይናው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ለተከታዮቹ አልኮል አጠጣጡን እያሳየ ህይወቱ አለፈ
በቻይና በማህበራዊ ሚዲያ የቀጥታ ስርጭቶች ላይ መወራረድ እየተለመደ መጥቷል
ግለሰቡ ሕይወቱ ያለፈው እስከ 60 በመቶ የአልኮል ይዘት ያለው ሶስት ጠርሙስ መጠጥ ከጠጣ በኋላ ነው
ቻይናው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ለተከታዮቹ አልኮል አጠጣጡን እያሳየ ህይወቱ አለፈ።
በቻይና ቲክቶክ መሳይ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ባይጁ የተሰኘ አልኮል የመጠጣት ውርርድ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል።
የዚህ አካል የሖነ ክስተትም በትናንትናው ዕለት ሳንኪነግ የተሰኘ ብዙ ተከታዮች ያሉት ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ እስከ 60 በመቶ የአልኮል መጠን ያለው መጠጥ የመጠጣት አቅሙን ለተከታዮቹ በማሳየት ላይ ነበር።
ይህ ግለሰብ አራት ጠርሙስ አልኮል መጠጣት እንደሚችል ለተከታዮቹ በማሳየት ላይ እያለ ሶስተኛውን ጠርሙስ እንደጨረሰ መውደቁ እና ከዚያም ወዲያው ህይወቱ ማለፉን ግሎባል ታየምስ ዘግቧል።
ይህ ስርጭት ብዙ ተመልካች ማግኘቱን ተከትሎ የሀገሪቱ ተቆጣጣሪ አካል ተንቀሳቃሽ ምስሉ እንዳይታይ ያደረገ ቢሆንም ጉዳዩ በቻይና የመከራከሪያ አጀንዳ ሆኗል።
ግለሰቡ ሌላኛው የቻይና ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ በቀጥታ ስርጭት ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽሞ ከተከታዮቹ እና ሌሎች ሰዎች አድናቆት ማግኘቱን ተከትሎ ድርጊቱን ለመፈጸም እንደተነሳሳ ተገልጿል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቻይና ተጸዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ የቀጥታ ስርጭቶችን በመጠቀም የተለያዩ ውርርዶችን የሚያካሂዱ ሲሆን ቻይናዊያን በጉዳዩ ዙሪያ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የተለያዩ የንግድ ተቋማትም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን በመጠቀም ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ በቀላሉ ብዙ ሀብት ሲያካብቱ መታየታቸው የቀጥታ ስርጭት ውርርዶች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
የቻይና ብሔራዊ ቪዲዮ እና ቴሌቪዥን አስተዳድር ከ31 በላይ አግባብ ያልሆኑ የቀጥታ ስርጭት ማህበራዊ ትስስር ገጾችን ማገዱ ተገልጿል።