ጀርመን የመጀመሪያውን “ግሪን ፊውል” ከኢምሬትስ ማግኘቷ አስታወቀች
ጀርመን ያጋጠማትን የነዳጅ ችግር ለመፍታት ነዳጅ ከኢምሬትስ ለመውሰድ የሚያችላት ስምምነት በቅርቡ መደረሱ የሚታወስ ነው፡
ጀርመን በ2025 የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ወደ "ዜሮ" የማውረድ አላማዋን ለማሳካት እየጣረች ነው
ጀርመን ለሃይል-ተኮር ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊ የሆኑትን የድንጋይ ከሰል እና ጋዝ ይተካልኛል ያለችውን የመጀመሪያን “አረንጓዴ ሃይድሮጅን (Green' Hydrogen )” ከኢምሬትስ ማግኘቷ አስታወቀች፡፡
ጀርመን በ 2025 የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ወደ "ዜሮ" የማውረድ አላማዋን ለማሳካት ቀደም ሲል ከሩሲያ ታገኝ የነበረውን የተፈጥሮ ጋዝ ለመተካት እየጣረች መሆኗ ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተከትሎ በሞስኮ ነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነችው ጀርመን የነዳጅ አቅርቦቷ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ጀርመን ለነዳጅ ድጎማ በሚል ከ60 ቢሊዮን በላይ ዩሮ ያወጣች ሲሆን በርካታ ተቋማት በነዳጅ አቅርቦት ላይ እንዲሰሩ በመወትወት ላይ ናት፡፡
የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያመለክተውም 13 ሜትሪክ ቶን አሞኒያ ያለው የመጀመሪያውን “አረንጓዴ ነዳጅ” ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ማግኘት ችላለች፡፡
ጀርመን ነዳጁን ልታገኝ የቻለችው የጀርመን ኢኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሃቤክ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የአየር ንብረት ልዑክ ሱልጣን አህመድ አል ጃብር እና ከጀርመናዊው የብረታ ብረት አምራች አውሩቢስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
የአውሮፓ ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው ጀርመን ያጋጠማቸውን ነዳጅ ችግር ለመፍታት ነዳጅ ከኢምሬትስ ለመውሰድ የሚያችላት ስምምነት መደረሱ የሚታወስ ነው።
ስምምነቱ የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ በቅርቡ አቡዳቢን በጎበኙበት ወቅት የተደረሰ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
የኢምሬትስ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሱልጣን አህመድ አል ጃበር እና መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ በተገኙበት የተፈረመው ስምምነት "በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአረብ ኢሚሬትስ እና የጀርመን የኢነርጂ አጋርነት የሚያጠናክር ነው" የተባለለትም ነበር፡፡
የአሁኑ የነዳጅ አቅርቦትም ታዲያ የተደረሰው ስምምነት የዚህ አካል ነው ተብሎለታል፡፡
በሌላ በኩል አረብ ኢሚሬትስ የነዳጅ ኩባንያ አድኖክ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በቀጥታ ናፍጣ ወደ ጀርመን የማድረስ ስራውን ያጠናቀቀ ሲሆን "በ2023 በወር እስከ 250ሺህ ቶን ናፍጣ ያቀርባል" ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡