ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ከቀድሞው መሪ ዙማ የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እናውላለን አሉ
ጃኮብ ዙማ የቀረበላቸውን የሙስና ክስ ውድቅ ማድረጋቸው አይዘነጋም
ዙማ ከ2009 እስከ 2018 በነበረው የስልጣን ዘመናቸው ሙስና ፈጽመዋል በሚል ተከሰዋል
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከእርሳቸው በፊት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በነበሩት ጃኮብ ዙማ የሙስና ምርመራ ዙሪያ ለቀረበላቸው ምክረ ሃሳብ ምላሻቸውን አቅርበዋል።
ከ2009 እስከ 2018 ባለው ጊዜ ዙማ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የከፍተኛ ደረጃ ዝርፊያ ውንጀላዎችን ለመመርመር የደቡብ አፍሪካ መንግስት የምርመራ ኮሚሽን ማቋቋሙ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም መሰረት የደቡብ አፍሪካ የፍትህ ኮሚሽን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ሰርተዋል የተባለውን የሙስና ምርመራ ሪፖርት ማቅረቡ ይታወቃል፡፡
ሪፖርቱ እንደሚያመላክተው ጃኮብ ዙማ በስልጣን ዘመናቸው አቱል እና ራጄሽ ጉፕታ ከተባለው ወንዳማማች ቱጃሮች ጋር ተመሳጥረው ሀብት አካብተዋል፡፡
ወንድማማቾቹ (አቱል እና ራጄሽ ጉፕታ) በፈረንጆቹ ከ2009 እስከ 2018 በስልጣን ላይ ከነበሩት ዙማ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ተጠቅመው ኮንትራት በመጨረስ፣ የመንግስትን ሀብት አላግባብ በመበዝበዝ፣በካቢኔ ሹመት ላይ ተጽእኖ በማሳደር እና የመንግስትን ገንዘብ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰው ከወራት በፊት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አይዘነጋም፡፡
ዙማ እና የጉፕታ ቤተሰብ ምንም አይነት ጥፋት እንዳልፈጸሙ ክሱን ውድቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ዙማ ባለፈው ዓመት የጉፕታ ቤተሰብ ላይ “አልመሰክርም ” በማለታቸው ብቻ ለ15 ወራት እስራት መዳረጋቸው የዚሁ ማሳያ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በጉዳይ ላይ ረዘም ያለ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ የመጨረሻውን የኮሚሽኑ ሪፖርት ተቀብለዋል፡፡
እንደ ኮሚሽኑ ሪፖርት ከሆነ፤ በመንግስት ባለቤትነት በተያዙ እንደ ሃይል አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እንዲሁም የጭነት እና ሎጅስቲክስ ቡድን ትራንስኔትን ጨምሮ በኢኮኖሚው ቁልፍ ዘርፎች የሙስና ወንጀል ተፈጽሟል፡፡
ሪፖርቱን የተመከቱት ፕሬዝዳንት ራማፎሳ መንግስት ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡
ራማፎሳ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ በላኩት ደብዳቤ የሰጡት ምላሽም መንግስት በወንጀል የተያዙ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች፣ የመንግስት ይዞታ እንዳይደገም እና ሰፋ ያለ የስርዓት ማሻሻያዎችን የሚዘረዝር ነው ተብሏል፡፡
ራማፎሳ በጉዳዩ ላይ ንግግር እንደሚደርጉም የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡