የጀርመን ወጣቶች ወደ መከላከያ ሰራዊት የመቀላቀል ፍላጎታቸው መቀነሱ ተገለጸ
ጀርመን የወታደሮቿን ቁጥር ማሳደግ ብትፈልግም የወጣቶቿ ፍላጎት ማነስ እንዳሳሰባት ገልጻለች
ጀርመን የወታደሮቿን ቁጥር ወደ 203 ሺህ ከፍ የማድረግ እቅዷ እንደማይሳካ አስታውቃለች
የጀርመን ወጣቶች ወደ መከላከያ ሰራዊት የመቀላቀል ፍላጎታቸው መቀነሱ ተገለጸ።
የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን ለዩክሬን ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ካዋጡ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ነች።
ሩሲያ ወደ ዩክሬን ጦሯን መላኳን ተከትሎ ጀርመን መከላከያ ሰራዊቷን የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አስታውቃለች።
ያሏትን የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን በመስጠቷ ካዝናዋ የተመናመነባት ጀርመን አዳዲስ ወታደሮችን እና ቴክኖሎጂን የመታጠቅ እቅድ አውጥታለች።
የሀገሪቱ የጦር አባላት ቁጥሯን አሁን ካለበት 183 ሺህ ከአምስት ዓመት በኋላ ወደ 203 ሺህ ከፍ የማድረግ እቅድ እንዳላት አስታውቃለች።
ይሁንና አዲስ የጦር አባላትን ለመመልመል የጀመረችው ትረት እንደማይሳካ ተገልጿል።
ጀርመናዊያን ወጣቶች የሀገሪቱን ጦር የመቀላቀል ፍላጎታቸው በ7 በመቶ ቅናሽ አሳይቷልም ተብሏል።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ እንዳሉት "ሁሉም ሰው በጀርመን መከላከያ ውስጥ የአዲስ ወታደሮች እጥረት እንዳለ ያወራል፣ ለዚህ ደግሞ ከእኔ በላይ ምስክር የለም" ብለዋል።
በጀርመን ላጋጠመው አዲስ ምልምል ወታደሮች እጥረት የበጀት እና የጦር መሳሪያ እጥረት ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑም ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ጦሩን የሚለቁ ወታደሮች መጠንም በ30 በመቶ ጨምራል የተባለ ሲሆን ሀገሪቱ ለገጠማት የወታደሮች ችግር ሌላኛው ምክንያት ነውም ተብሏል።