“መንግስት ረስቶናል፤ የእስር ቤት በር የሚከፈትልን ሰው ሲሞት ብቻ ነው” ሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች
“ዜጎቼን አልረሳኋቸውም” ያለው የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በቅርቡ መመለስ እንደሚጀምር ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቋል
ስደተኞቹ የሳዑዲ ፖሊስ እንዲለቃቸው ሲጠይቁ ‘መንግስታችሁ ጦርነት ላይ ነን ብሎናል’ የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል
በሳኡዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች “መንግስት ረስቶናል” ሲሉ ተናገሩ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በተለያዩ መንገዶች በመናገር ላይ ናቸው፡፡
አል ዐይን አማርኛ ጥቆማው በሚላኩለት መልዕክቶች እና በተለያዩ መንገዶች ከደረሰው በኋላ ስደተኞቹን ለማነጋገር ጥረት አድርጓል፡፡
መዲና ኑሪ በሳዑዲ እስር ላይ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መካከል አንዷ ናት፡፡
በሪያድ ከነ ልጇ ታስራ አንድ ዓመት እንዳለፋት የተናገረችው መዲና ህጻናት በረሃብ እና በበሽታ ህይወታቸው ሲያልፍ በዚያው በእስር ቤት ሆና መመልከቷን ለአል ዐይን አማርኛ በላከችው የድምጽ መልዕክት ገልጻለች፡፡
“በአንድ ከፍል ውስጥ እስከ 500 ሰዎች ባንድ ላይ ታስረናል፣ምግብ በቀን አንዴ ጊዜ ብቻ ይሰጠናል እሱም በቂ አይደለም” የምትለው መዲና “የልጄ ጤና በየቀኑ እየተባባሰ ነው እንዳላጣት ፈርቻለሁ” ስትልም አክላለች፡፡
በሳዑዲ ሺመሺ እስር ቤት ከታሰረች አንድ ዓመት ሊሞላት መሆኑን ለአል ዐይን በላከችው የድምጽ መልዕክት የገለጸችው ሙኒራ ጀማል ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ ናት፡፡
ከታሰረችበት ጊዜ ጀምሮ የሳዑዲ ፖሊስ የሰጣትን አንድ ልብስ ብቻ እንደለበሰች የምትናገረው ሙኒራ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳልደገፋቸው ትናገራለች፡፡
“በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ እየረዳን አይደለም፡፡ በየቀኑ ልጆቹ እየሞቱ ነው፡፡ በር የሚከፈትልን ሰው ሲሞት ብቻ ነው፡፡ ፖሊሶች ሰው ታሟል ብላችሁ በር እንዳታንኳኩ ብለውናል” የምትለው ሙኒራ “የኢትዮጵያ መንግስት ረስቶናል” ብላለች፡፡
በእስር ቤቱ ቀን ቀን ከፍተኛ ሙቀት ሌሊት ደግሞ ከፍተኛ ቅዝቃዜ መኖሩን የምትናገረው ሙኒራ ከረሃቡ በተጨማሪ “ይህንን መቋቋም አልቻልንም” ትላለች፡፡
ለአል ዐይን አማርኛ መልዕክት የላከው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሸሪፍ ሲራጅ ነው፡፡ በሳዑዲ ሸሜቲ ካምፕ በእስር ላይ እንደሚገኝ የሚናገረው ሸሪፍ ሲራጅ በሳዑዲ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስልክ ሲደወል ኤምባሲው ስልክ እንደማይመልስ ይገልጻል፡፡
ስልክ የምደውለው በካምፑ ምግብ የሚያቀርቡ የባንግላንዴሽ ሰራተኞችን በመለመን ነው የሚለው ሸሪፍ ሸሜቲ ካምፕ ከ30-40ሺ የሚደርሱ ስደተኞች የሚገኙበት ትልቅ ካምፕ መሆኑን ገልጿል፡፡
በካምፑ ውስጥ በተለይ ህጻናትና ሴቶች ጸሃይ እየመታቸው እንደሆነ የገለጸው ሸሪፍ የኢትዮጵያ መንግስት በቶሎ ወደ ሃገራቸው እንዲመልሳቸው ጠይቋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት በሳዑዲ መንግስትና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በተደረገ ትብብር ከ40 ሺህ በላይ ስደተኞችን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ በፊት መናገሩ ይታወሳል፡፡
ሸሪፍ በመጀመሪያው ዙር እድሉ እንዳልደረሰውና አሁን የመመለሱ ሂደት መቆሙን ይናገራል፡፡
ስደተኞቹ የሳዑዲ መንግስትን ሲጠይቁ “የሚወስድ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ይወሰዳችሁ፣ እኛ እናንተን አስረን ማቆየት አንፈልግም፣ የሀገራችሁ መንግስት ጦርነት ላይ ነኝ ብሎ እየተቀበለ አይደለም” የሚል መልስ እንደሚሰጣቸው ነው የሚናገረው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በእስር ላይ ያሉ ዜጎችን ወደ አገራቸው ሲመልስ መቆየቱን አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው የመመለሱ ሂደት አለመቆሙን ጠቁመው የተወሰነ መቀዛቀዝ ግን ነበር ብለዋል፡፡
ይሁንና እንደከዚህ በፊቱ በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡
በመሆኑም በቅርቡ በሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው የመመለሱ ዘመቻ ይጀመራል ብለዋል አምባሳደር ዲና፡፡