በአይጥ መንጋ የተማረረችው የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ ለአይጦች የወሊድ መከላከያ ልትሰጥ ነው
በ2023 የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በከተማዋ ከ3 ሚሊየን በላይ አይጦች ይገኛሉ
አይጦችን በመርዝ መግደል የሚፈጥረውን ብክለት ለመከላከል ነው የወሊድ መከላከያን በመፍትሄነት የቀረበው
በአይጥ መንጋ የተቸገረችው ግዙፏ ሜትሮፖሊታን ከተማ ኒውዮርክ የወሊድ መከላከያዎችን ለአይጦች ልትሰጥ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በሙከራ ደረጃ ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል በተባለው የመፍትሄ ሀሳብ በርካታ አይቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የወሊድ መቆጣጠርያ ክኒኖችን በምግብ ውስጥ በመደበቅ አይጦች እንዲመገቡት ይደረጋል ተብሏል፡፡
ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ በአይጥ መንጋ እየደረሰ በሚገኝው ጥፋት እና በሰዎች ላይ እያስከተሉ ከሚገኙት የጤና እክል ጋር በተያያዘ የከተማዋ ከንቲባ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች በተካፈሉበት ስብሰባ ላይ የአይጦችን ቁጥር ለመቀነስ በመርዝ እና በተለያዩ መንገዶች ለማጥፋት የመፍትሄ ሀሳብ ቀርቦ ነበር፡፡
ሆኖም ከአይጦቹ ከፍተኛ ቁጥር ጋር በተያያዘ በመርዝ መግደል በጤና እና በአካባቢ ላይ ከሚያስከትለው ብክለት ጋር በተያዘ እንዲሁም የሞቱ አይጦችን በሚመገቡ እንስሳት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ የወሊድ መከላከያው የተሻለ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል፡፡
በዚህ ዙርያ የሚሰሩ ባለሙያዎች በ2025 12 ወራት ውስጥ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ውስጥ ክኒኖቹን በማስቀመጥ ምን ያህል መድሀኒቶች በአይጦቹ እንደተወሰዱ በመከታተል የመራባት ምጣኔያቸውን ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
“ሴኔስ ቴክ” የተባለው የወሊድ መቆጣጠርያ መድሀኒቱን የሚያመርተው ኩባንያ እንዳስታወቀው መድሀኒቱን የሚወስዱ አይጦች ለ45 ቀናት ያህል እንዳይራቡ የሚያደርጋቸው ነው፡፡
በኒውዮርክ የሚርመሰመሱ አይጦች ለነዋሪዋቿ እና ለከተማዋ አስተዳደር እራስ ምታት ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡
የከተማዋ ጤና ተቋማት ከአይጦች እና ከሌሎች ነፍሳት ጋር በተገናኘ የሚከሰተው “ሌፕቶስፓይሮሲስ” የተሰኝው በሽታ እየተበረካተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
“ሌፕቶስፓይሮሲስ” ከአይጦች እና ከሌሎች እንሳስት በሚወጡ ፈሳሾች ከተበከለ ውሀ፣ አፈር እና ምግብ ጋር በሚኖር ንክኪ የሚፈጠር ባክቴርያ ሲሆን ምልክቶቹ የሆድ ህመም፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣እራስ ምታት እና የጡንቻ ህመም ናቸው፡፡
በ2023 መጨረሻ የወጡ መረጃዎች በኒውዮርክ ሶስት ሚልየን አይጦች እንደሚኖሩ ሲጠቁሙ 7 ሚሊየን 931 ሺህ ሰዎች በሚገኙባት ከተማ የአይጦች ቁጥር አጠቃላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ቁጥር ግማሽ ለመድረስ የተቃረበ ነው፡፡
ሆኖም ኒውዮርክ ከአሜሪካ ከተሞች በአይጦች ብዛት ቀዳሚዋ አይደለችም ይህን ደረጃ ይዛ የምትገኝው ቺካጎ ስትሆን ሎስአንጀልስ ደግሞ ሁለተኛ ነች፡፡
በአለምአቀፍ ደረጃ የህንዷ ዴሽኖክ ከተማ እና የእንግሊዟ ለንደን የቀዳሚ እና ተከታዩን ስፍራ ይዘዋል፡፡
ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ የፍቅር ከተማ ተብላ የምትጠራው የፓሪስ ነገር ነው በፓሪስ 2ሚልየን 100ሺህ ሰዎቸ ሲኖሩ የአይጦች ቁጥር ደግሞ 6 ሚልየንን ይሻገራል፡፡