አሜሪካ እና ብሪታኒያ በናይጄሪያ ዋና ከተማ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል አስጠነቀቁ
የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳየ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም
ጥቃቱ በመንግስት ህንጻዎች፣ የአምልኮ ቦታዎች እና ትምህርት ቤቶች ላይ ያነጣጠረ ሊሆን ይችላል ተብሏል
አሜሪካ እና ብሪታንያ እሁድ እለት በናይጄሪያ የፌዴራል ዋና ከተማ አቡጃ በተለይም በመንግስት ህንጻዎች፣ የአምልኮ ቦታዎች እና ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ኢላማዎች ላይ ያነጣጠረ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ናይጄሪያ በዋነኛነት በሰሜናዊ ምስራቅ እስላማዊ አማጽያን እየተዋጋች ቢሆንም አማጽያኑ የሚያደርሱት ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ ስጋት እየጫረ መጥቷል፡፡
በተለይም ባሳለፍነው ወርሃ ሐምሌ ላይ እስላማዊ አማጽያኑ በአቡጃ በሚገኝ እስር ቤት ላይ ለተፈጸመውና 440 የሚጠጉ እስረኞችን እንዲያመልጡ ምክንያት ለሆነው ጥቃት ሃላፊነቱ መውሰዱን ደግሞ ናይጄሪያ ትልቅ አደጋ እንደተጋረጠባት አማላካች መሆኑ በመነገር ላይ ነው፡፡
እናም በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ የሽብር ጥቃት ሊሰርስ እንደሚችል አሜሪካ እና ብሪታንያ በትናንትናው እለት አስጠንቅቀዋል፡፡
በናይጄሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ “በናይጄሪያ በተለይም አቡጃ ውስጥ የሽብር ጥቃት ከፍተኛ ስጋት አለ” ብሏል፡፡
የብሪታኒያ መንግስት በበኩሉ በናይጄሪያ የሚገኙ ዜጎቹ “በአቡጃ እየደረሰ ያለው የሽብር ጥቃት ስጋት” ነቅተው እንዲጠብቁ ማስጠንቀቁ ሮይተርስ ዘግቧል።
"ጥቃቱ ምዕራባውያን ላይ ያተኮረ እንዲሁም ቱሪስቶች የሚጎበኙዋቸውን ቦታዎችን ሊጎዳ ይችላል"ብሏል የብሪታኒያ መንግስት፡፡
አሜሪካ እና ብሪታኒያ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ቢያስጠነቅቁም በናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡
በመላ ናይጄሪያ የተስፋፋው የጸጥታ ችግር ጉዳይ በመጪው የካቲት ወር በሚካሄደው ምርጫ ለሚሳተፉ የሀገሪቱ ዜጎች ሙሃመዱ ቡሃሪ ለሚተካውን አዲስ ፕሬዝዳንት በአደራነት የሚሰጡት አንገብጋቢና ዐቢይ የቤት ስራ ነው፡፡