ፕሬዝዳንት ዢ “ቻይናና ጀርመን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አብረው መሥራት አለባቸው” አሉ
የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ከአውሮፓ ሀገራት ተቃውሞ የገጠመውን የቻይና ጉብኝት ጀምረዋል
የጀርመኑ ኦላፍ ሾልዝ ከቻይናው ዢ ጂንፒንግ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል
የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ከአውሮፓ ሀገራት ተቃውሞ የገጠመውን የቻይና ጉብኝት መጀመራው ተገለፀ።
መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ከፍተኛ የንግድ ልኡካን ቡድንን ይዘው ወደ ቻይና ያመሩ ሲሆን፤ ይህ ጀርመን ከቤጂንግ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማሳደግ የሰጠችውን ትኩረት ያሳያል ተብሏል።
የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በዛሬው እለትም ከቻይናው ፕሬዝዳት ዢ ጂን ፒንግ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የቻይናው ሲሲቲቪ ዘግቧል።
በውይይቱ ወቅትም የቻይናው ፕሬዝዳት ዢ ጂን ፒንግ፤ “ትልቅ ተፅዕኖ ያላቸው ቻይና እና ጀርመን በበዚህ የለውጥ እና ግርግር ጊዜ ለዓለም ሰላም ሲሉ በጋራ መስራት አለባቸው” ብለዋል።
የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በበኩላቸው ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት እና በዓለም አቀፍ ህጎችና ስርዓቶች ላይ አደጋ በተጋረጠበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ፕሬዝዳት ዢ ጂን ፒንግ ጋር በአካ ተገናኝተው መምከራው መልካ አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል።
የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የቻይና ጉብኝት ከአውሮፓ ሀገራት ተቃውሞ እንደገጠመው ይታወሳል።
ጀርመን ከቻይና ጋር ጥብቅ የንግድ ግንኙነት ካላቸው የአውሮፓ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ስትሆን ይህ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስሯ ግን በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት እንዳልተወደደላት ተገልጿል።
የቻይናው የሎጅስቲክ ኩባንያ ሲስኮ በአውሮፓ ካሉ ግዙፍ ወደቦች መካከል አንዱ የሆነው ሀምቡርግ ወደብን የ35 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ የወጣውን ጨረታ አሸንፏል።
ይሄንን ተከትሎም የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ጀርመን ለቻይናው ሲስኮ ኩባንያ የሀምቡርግ ወደብን ሽያጭ እንድትሰርዝ በመወትወት ላይ ናቸው።
የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካንን ጨምሮ የቡድን ሰባት ሀገራት የቻይናን ተጽዕኖ ለመመከት 300 ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደባቸው አይዘነጋም።