ጀርመን ጦሯን ለማስታጠቅ 20 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚያስፈልጋት ገለጸች
ቢዝነስ ኢንሳይደር ከሆነ የጀርመን ጦር እጁ ላይ ያሉት የጦር መሳሪያዎች ለሀለት ቀናት ውጊያ ብቻ የሚበቁ እንደሆኑ ተገልጾ ነበር
ጀርመን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መለገሷን ተከትሎ ጦሯ የመሳሪያ እጥረት ገጥሞታል ተብሏል
ጀርመን ጦሯን ለማስታጠቅ 20 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚያስፈልጋት ገለጸች፡፡
የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን ብሄራዊ ጦሯ የጦር መሳሪያ እጥረት እንደገጠመው ቢልድ የተሰኘው የሐገሪቱ ጋዜጣ የምክር ቤቱን ኮሚሽነር ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ቡንደስዌር የተሰኘ ስያሜ ያለው የጀርመን ጦር ያለውን የጦር መሳሪያ ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን መለገሱን ተከትሎ አሁን ላይ የጦር መሳሪያ ክምችቱ ተመናምኗል፡፡
የመከላከያ ምክር ቤት ኮሚሽነር የሆኑት ኤቫ ሆግል እንዳሉት የጀርመን ጦር ከዚህ በፊትም የጦር መሳሪያ እጥረት ቢኖርበትም ለዩክሬን መለገሱ ግን የመሳሪያ ክምችት እጥረቱን እንዳባባሰው ገልጸዋል፡፡
የጀርመን ጦር ከዘመናዊ እስከ መሰረታዊ የጦር መሳሪያ እጥረት እንዳጋጠመው የተናገሩት ኮሚሽነሯ በአጠቃላይ ይሄንን ችግር ለመፍታት 20 ቢሊዮን ዩሮ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
የጦር መሳሪያው በጀርመን በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የሀገሪቱ ጦር ብቻ ሳይሆን በኔቶ ስራ የተሰማራው የሀገሪቱ ጦር በተለይም በሉትንያ የሰፈረው ጦር የጥይት መከላከያ ሳይቀር ብዙ ተመሳሳይ ችግር እንዳለበት ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ የጀርመን ጦር በሚገባ ሊታጠቅ ይገባል የሚሉት ኮሚሽነሯ የጦሩ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ደረጃው ዝቅ ከማለቱ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ የጀርመን ተሳትፎ እየቀነሰ ሊሄድ ይችላም ብለዋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት ቢዝነስ ኢንሳይደር እንደዘገበው ከሆነ የጀርመን ጦር እጁ ላይ ያሉት የጦር መሳሪያዎች ለሀለት ቀናት ውጊያ ብቻ የሚበቁ እንደሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
ጀርመን ለዩክሬን ሶስት የአየር መቃወሚያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ለመለገስ ቃል የገባች ሲሆን እስካሁን አንዱ ለኬቭ ሲተላለፍ ሁለቱ ደግሞ በፈረንጆቹ 2023 ላይ እንደሚሰጡ አስታውቃለች፡፡
የአውሮፓ ህብረት ባሳለፍነው ሳምንት እንዳሳወቀው የህብረቱ አባል ሀገራት እጃቸው ላይ ያለውን የጦር መሳሪያ ለዩክሬን መለገሳቸውን ተከትሎ የጦር መሳሪያ እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡
ሀገራቱ ይሄንን የጦር መሳሪያ እጥረት ለመፍታት የ70 ቢሊዮን ዩሮ የግዢ እቅድ ይፋ ያደረገ ሲሆን ሀገራት ብሄራዊ ደህንነታቸውን በማይጎዳ መንገድ ለዩክሬን ድጋፍ እንዲያደርጉ ማሳሰቡም ይታወሳል፡፡