በበርሊን የሩሲያ አምባሳደር ጀርመን ለዩክሬን ያቀረበቻቸው የጦር መሳሪያዎች ነጹሃን እየተጎዱበት ነው ብለዋል
ጀርመን ለዩክሬን የጦር መሳሪያዎችን በመላክ ቀይ መስመር እየጣሰች ነው ሲሉ በበርሊን የሩሲያ አምባሳደር አስጠነቀቁ።
በጀርመን የሩሲያ አምባሳደር ሰርጌይ ናቼቭ፤ የዩክሬን መንግስት ጀርመን ስሪት አውዳሚ ጦር መሳሪያዎችን እየታጠቀ መሆኑ ሀቅ ነው ብለዋል።
ነገር ግን በእነዚህ የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ጦር ላይ ብቻ ሳይሆን በዶንባስ ክልል በሚገኙ ንጹሃን ዜጎችን ለማጥቃት እየዋሉ ነው፤ ይህ ደግሞ ቀይ መስመርን መጣስ ነው ማለታቸውን አር.ቲ ዘግቧል።
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ሀገራቸው ለዩክሬን አዲስ የጦር መሳሪያ ልታበረክት መሆኑን እና በቅርቡ እንደሚላክላት መናገራቸው ይታወሳል።
አዲሱ የጦር መሳሪያ “ሱፐር ሞዴል ዊፐን” በመባል እንደሚጠራም መራሄ መንግስቱ የተናገሩ ሲሆን፤ በተጨማሪም ትልቅ የአየር መከላከያ ስርዓት፤ ራዳር እና ድሮኖች ለዩክሬን እንደሚላኩ አረጋግጠዋል።
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ሃምሌ ላይ በዩክሬን ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ሀገራቸው ዩክሬንን ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን ለፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በገልጸውላቸዋል።
ዩከሬን እና ሩሲያ ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተከትሎ የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ጀርመንም ለዩክሬን ጦር መሳሪያ ለማቅረብ በሚል ፖሊሲ እስከ ማሻሻል ደርሳ እንደነበረ ይታወሳል።
ሩሲያም በተለያዩ ጊዜያት ከምእራባውያን ለዩክሬን ያበረከቷቸው የረጅም ርቀት ሮኬትን ጨምሮ ይለያዩ የጦር መሳሪያዎችን አወደምኩ ማለቷ አይዘነጋም።