ኢራን በእስራኤል ላይ የምትፈጽመውን የሚሳይል ጥቃት ማጠናቀቋን ገለጸች
ኢራን እስራኤል ለተጨማሪ የበቀል እርምጃ ካልጋበዘቻት በስተቀር እርምጃዋን ማጠናቀቋን አስታውቃለች
እስራኤል እና አሜሪካ በቴህራን ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ዝተዋል
ኢራን በእስራኤል ላይ የምትፈጽመውን የሚሳይል ጥቃት ማጠናቀቋን ገለጸች።
ኢራን በእስራኤል ላይ የምትፈጽመውን የሚሳይል ጥቃት ማጠናቀቋን በዛሬው እለት ስትገልጽ፣ እስራኤል እና አሜሪካ በቴህራን ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ዝተዋል።
ዋሽንግተን እንደገለጸችው ኢራን ለፈጸመችው የሚሳይል ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ከረጅም ጊዜ የመካከለኛው ምስራቅ አጋሯ እስራኤል ጋር እየሰራች ነው።
ኢራን በዚህ ጥቃት 180 ሚሴይሎችን መጠቀሞን እስራኤል ገልጻለች።
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ ለመሞከር በዛሬው እለት ስብሰባ የጠራ ሲሆን የአውሶፓ ህብረት ደግሞ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
"የእስራኤል አገዛዝ ተጨማሪ የበቀል እርምጃ እንድንወስድ ካልጋበዘን በስተቀር እርምጃችንን አጠናቀናል። እንደዚያ የሚሆን ከሆነ ምላሻችን ኃይለኛ እና ጠንካራ ይሆናል" ሲሉ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አባስ አርቃቺ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
በቤሩት የምታደርገውን የአየር ጥቃት ዛሬ ማለዳ በድጋሚ የጀመረችው እስራኤል በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላ መሽጎባቸዋል ባለቻቸው በቤሩት ከተማ ደቡባዊ ዳርቻ ባሉ ቦታዎች ላይ ቢያንስ 12 ጊዜ ድብደባ አድጋለች።
የኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችው ጥቃት
ኢራን ትልቅ የተባለውን ጥቃት በእስራኤል ላይ አድርሳለች። በመላው እስራኤል የማስጠንቀቂያ ደዎሎች ተደውለዋል፤ በኢየሩሳሌም እና በዮርዳኖስ ወንዝ ሸለቆዎች ከፍተኛ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል። አጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝብ ከብምብ ጥቃት ሊያድኑ ወደሚችሉ መጠለያዎች እንዲገባ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር።
የእስራኤል ባለስልጣናት በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለችው ዌስትባንክ አንድ ሰው መገደሉን ገልጸዋል። እስራኤል ውስጥ የደረሰ ጉዳት መኖሩን የሚያሳይ ሪፖርት እስካሁን አልወጣም።
ኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችው ጥቃት ራሷን ለመከላከል እና ኢላማ ያደረገችውም በወታደራዊ መሰረተልማቶች ላይ መሆኑን ገልጻለች። ኢራን በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሶሰት ወታደራዊ ሰፈሮችን ኢላማ ማድረጓን ሮይተርስ የኢራን መንግስት መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ቴህራን ጥቃቱን የፈጸመችው እስራኤል በሊባኖስ ላይ ለፈጸመችው ወረራ እና ለሄዝቦላ እና ሀማስ አመራሮች ግድያ ምላሽ ለመስጠት ነው።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኒኤል ሀጋሪ በኤክስ ገጻቸው ኢራን ካስወነጨፈቻቸው ሚሳይሎች ውስጥ አብዛኞቹን ከሽፈዋል ብለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "ኢራን ትልቅ ስህተት ሰርታለች፣ዋጋ ትከፍላለች" ሲሉ ዝተዋል።
የኢራን ጦር ባወጣው መግለጫ እስራኤል ልትፈጽም የምትችለው ማንኛውም ጥቃት ከባድ አፈጸፋ ይከተለዋል ብለዋል።
ኢራን እና አሜሪካ ወደ ቀጥተኛ ግጭት ይገባሉ የሚለው ስጋት እየጨመረ መጥቷል።