ኔቶ አመታዊ የኑክሌር ጦር መሳርያ ልምምድ ሊጀምር ነው
ድርጅቱ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ልምምዱን የሚያደርገው ከሩስያ 900 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የውሀ ክፍል ላይ ነው
በልምምዱ ከ13 ሀገራት የተውጣጡ 60 የኑክሌር አረር መሸከም የሚችሉ የጦር አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ይውላሉ
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ለአስርተ አመታት ሲመክርበት የቆየውን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልምምድ ከመጪው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ ሊያካሂድ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ለሁለት ሳምንታት የሚቆየው ልምምድ በቤልጂየም እና ኔዘርላንድ የሚመራ ሲሆን 8 የጦር ካምፖችን ፣ 2ሺህ ወታደሮችን እና ከ13 ሀገራት የተውጣጡ 60 የጦር አውሮፕላኖችን ጥቅም ላይ እንደሚያውል ተሰምቷል፡፡
የኑክሌር አረር መሸከም የሚችሉ ሮኬቶችን የታጠቁ ቦምብ ጣይ እና የውጊያ ጄቶች እንደሚሳተፉበት በተገለጸው ልምምድ ትክክለኛ የኑክሌር አረረ በሮኬቶቹ ላይ እንደማይገጠም ተገልጿል፡፡
ላለፉት አስረተ አመታት ወደ ተግባራዊነት እንዲቀየር በደርጅቱ አባል ሀገራት እና አመራሮቹ ዘንድ ሲመከርበት የቆየው የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልምምድ ሩስያ የኑዩክሌር አያያዝ እና አጠቃቀም ፖሊሲዋ ላይ ለውጥ አደርጋለሁ ማለቷን ተከትሎ ወደ ገቢራዊነት እንዲገባ መወሰኑን የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩት ተናግረዋል፡፡
ልምምዱ ከሩሲያ 900 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ሰሜን ባሀር የውሀ ክልል ላይ የሚደረግ ሲሆን የሞስኮ ባለስልጣናት ጉዳዩን በደብዳቤ እንዲያውቁት መደረጉ ተገልጿል፡፡
አዲሱ የደርጅቱ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ልምምዱን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፤ "እርግጠኛ መሆን በማይቻልበት አለም ውስጥ መከላከያችንን መፈተሽ እና ማጠናከር አስፈላጊ ነው፤ ይህም ጠላቶቻችን ኔቶ ዝግጁ እንደሆነ እና ለማንኛውም ስጋት ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እንዳለው እንዲገነዘቡ ይረዳል" ብለዋል፡፡
የኔቶ ምክትል ዋና ጸሀፊ አንገስ ላፐስሊ በበኩላቸው “ኔቶ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ሃይል መፈርጠም ፣የቻይናን የኑክሌር አቅም መስፋፋት እና የኢራንን እንቅስቃሴ ሲከታተል ቆይቷል፤ ከሁሉም የሚያሳስበን ግን ሩሲያ ነች” ብለዋል።
በተጨማሪም ሞስኮ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኑክሌር ጦር መሳርያዎቿ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት እያደረገች መሆኗን ገልፀው በአጭር እና መካከለኛ ርቀት የጦር መሣሪያ ስርዓቶች ላይ የበለጠ ትኩረት መስጠቷን ተናግረዋል።
ድርጅቱ ከሩሲያ በኩል እየበረከቱ የመጡ የኒዩክሌር ጦር መሳርያዎች ዛቻ እና ከዩክሬን ጋር እየተደረገ የሚገኘው ጦርነት የመቀዛቀዝ ምልክት አለማሳየት ስትራቴጂዎችን እንዲያጤን እንዳስገደደው ኤፒ ዘግቧል፡፡
በመጪው ሰኞ ይጀመራል የተባለው የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልምምድም ድርጅቱ እና አባል ሀገራቱ በተለይ በኑክሌር ጦር መሳርያ በኩል ያላቸውን የውግያ አቅም ለመፈተሸ እና ለማሳየት የሚጠቀሙበት እንደሆነ ተነግሯል፡፡