አረብ ኢምሬትስ ለጀርመን ነዳጅ ልታቀርብ ነው
የኢምሬትስ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አል ጃበር ስምምነቱ "የሀገራቱ የኢነርጂ አጋርነት የሚያጠናክር ነው" ብለውታል
በሞስኮ ነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነችው ጀርመን የነዳጅ አቅርቦቷ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል
የአውሮፓ ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው ጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ያጋጠማቸውን ነዳጅ ችግር ለመፍታት በሚል አረብ ኢምሬትስን ጨምሮ ሶስት የባህረ ሰላጤ ሀገራትን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡
ኦላፍ ሾልዝ ጀርመን ቀደም ሲል ከሩሲያ ታገኝ የነበረውን ነዳጅ ለመተካት የሚያስችላቸው መፍትሄ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አረብ ኢምሬትስ ለጀርመን ነዳጅ ለማቅረብ ከስምምት መደረሱ ተገልጿል፡፡
የኢምሬትስ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሱልጣን አህመድ አል ጃበር፤ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ በተገኙበት የተፈረመው ስምምነት "በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአረብ ኢሚሬትስ እና የጀርመን የኢነርጂ አጋርነት የሚያጠናክር ነው" ብለውታል፡፡
ሾልዝ የኢነርጂ ስምምነቱ እንደተቀበሉት መናገራቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
አረብ ኢሚሬቶች የነዳጅ ኩባንያ አድኖክ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በቀጥታ ናፍጣ ወደ ጀርመን የማድረስ ስራውን ያጠናቀቀ ሲሆን "በ2023 በወር እስከ 250ሺህ ቶን ናፍጣ ያቀርባል" ተብሏል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተከትሎ በሞስኮ ነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነችው ጀርመን የነዳጅ አቅርቦቷ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ጀርመን ለነዳጅ ድጎማ በሚል ከ60 ቢሊዮን በላይ ዩሮ ያወጣች ሲሆን በርካታ ተቋማት ሀገራቸው በነዳጅ አቅርቦት ላይ እንዲሰራ በመወትወት ላይ ናቸው፡፡
ይሄንን ተከትሎም በርሊን ኢኮኖሚዋ እንዳይጎዳ የነዳጅ አቅርቦት ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለማግኘት ጥሪዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ለዚህም የሀገሪቱ መራሄ መንግስትም በነዳጅ የበለጸጉ የአረብ ሀገራት ነዳጃቸውን ወደ በርሊን ሊልኩ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ለመወያየት በባህረ ሰላጤው ሀገራት ጉብኝት በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡