እስራኤል የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህን ኢላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሟ ተነገረ
ለሄዝቦላህ ቅርበት ያላቸውና የኢራን መገናኛ ብዙሃን ናስራላህ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው እየዘገቡ ነው
ኢራን፥ እስራኤል በቤሩት እየተፈጸመችው ያለው ድብደባ “ቀይ መስመሩን ያለፈ ነው” ብላለች
እስራኤል በሊባኖስ መዲና በትናንትናው እለት የፈጸመችው ድብደባ በሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ ላይ ያነጣጠረ ነበር ተባለ።
ቴል አቪቭ የአየር ጥቃቱ ናስራላህ ላይ ኢላማ ስለማድረጉ እስካሁን ማረጋገጫ ባትሰጥም ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የእስራኤል ባለስልጣን የሄዝቦላህ ማዘዣ ጣቢያ እኛ በመሪው ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ስለመፈጸሙ ተናግረዋል።
“ምንም እንኳን (ናስራላህ) እንዲህ ሆኗል ለማለት ጊዜው ባይሆንም አንዳንድ ጊዜ ስኬታማ ስንሆን ነገሮችን ለመሸፋፈን ይሞክራሉ” በማለትም በአየር ድብደባው ናስራላህ ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዳልቀረ አመላክተዋል።
የሊባኖሱ አል ማናር ቴሌቪዥን የሄዝቦላህ አመራሮች በተደጋጋሚ ይገኙበታል በተባለው አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት ሰባት ህንጻዎች መፈራረሳቸውን ዘግቧል።
ሄዝቦላህ እስካሁን መሪው ስለሚገኙበት ሁኔታ እስካሁን በይፋ መግለጫ አላወጣም።
የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል በበኩሉ ናስራላህ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበትና ቴህራን የሚገኝበትን ሁኔታ እየተከታተለች መሆኑን ዘግቧል።
የሄዝቦላህን የሚሳኤል ክፍል ሃላፊ ሙሀመድ አሊ ኢስማኤል እና ምክትሉን ሆሴን አህመድ ኢስማኤል መግደሏን ያስታወቀችው እስራኤል በዛሬው እለትም በቤሩት ዙሪያ ድብደባዋን ማጠናከሯን ሬውተርስ ዘግቧል።
ለአምስት ስአታት ከ20 በላይ የአየር ድብደባዎች መፈጸማቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያን ቤታቸው ለቀው በአደባባዮች እና ፓርኮች ተሰብስበዋል ነው የተባለው።
የእስራኤል ጦር ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ 10 ሮኬቶች ከሊባኖስ ወደ እስራኤል መተኮሳቸውንና “የተወሰኑት” ተመተው መውደቃቸውን ገልጿል። ይሁን እንጂ ምን ያህሎቹ ኢላማቸውን መተው ጉዳት እንዳደረሱ በዝርዝር አልጠቀሰም።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር በትናንቱ ጥቃት ስድስት ሰዎች መሞታቸውንና ከ91 በላይ መቁሰላቸውን ያመላከተ ሲሆን፥ በአንድ ሳምንት ውስጥ የሞቱ ሊባኖሳውያን ቁጥር ከ700 ተሻግሯል።
የትናንቱን የቤሩት ጥቃት “ቀይ መስመሩን ያለፈ ነው” ያለችው ኢራን፥ እስራኤል የአሜሪካን ቦምቦች በመጠቀም ሊባኖስን እያወደመች ነው ስትል ከሳለች።
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን ግን ዋሽንግተን “በንከር በስቲንግ” የተሰኙት ቦምቦች ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት በቴል አቪቭ አልተነገሯትም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በ79ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ “ሄዝቦላህ ጦርነትን እስከመረጠ ድረስ እስራኤል ምርጫ የላትም” የላትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከኒውዮርክ ወደሀገራቸው ተመልሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሄዝቦላህ የእስራኤል የደህንነት ስጋት እስከማይሆንበት ድረስ በሊባኖስ የቡድኑ ይዞታዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ይቀጥላል ማለታቸውም እስራኤልና ሄዝቦላህ ከ18 አመት በኋላ ወደለየለት ጦርነት መግባታቸው አይቀሬ መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል።