የአውሮፓ መሪዎች የሰላም ስምምነት ሳይደረስ የሚደረግ የዩክሬን ተኩስ አቁም አደገኛ ነው ሲሉ አስጠነቀቁ
ማክሮን ይህን ስብሰባ የጠሩት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ዩክሬንንና አውሮፓውያንን ያገለለ ንግግር ካመቻቹ በኋላ ነው

የአሜሪካና የሩሲያ ባለስልጣን በዩክሬን ጉዳይ የሚያደርጉት የመጀመሪያው ስብሰባው በዛሬው እለት በሳኡዲ አረቢያ እንደሚጀመር ይጠበቃል
የአውሮፓ መሪዎች የሰላም ስምምነት ሳይደረስ የሚደረግ የዩክሬን ተኩስ አቁም አደገኛ ነው ሲሉ አስጠነቀቁ።
የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ቡድን በትናንትናው እለት በፓሪስ ባደረገው ስብሰባ ለዩክሬን የጸጥታ ዋስትና እንዲሚሰጥ ገልጾ፣ የሰላም ስምምነት ላይ ሳይደረስ የሚረግ ተኩስ አቁም ግን አደገኛ ነው ማስጠንቀቁን ሮይተርስ የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ባለስልጣኑ የፓሪሱን ስብሰባ ውጤት ሲያጠቃልሉ "አሜሪካ በምትሰጠው ድጋፍ ላይ በመነሳት የደህንነት ዋስትና ለመስጠት ዝግጁ ነን" ብለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ይህን ስብሰባ የጠሩት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዩክሬንንና አውሮፓውያንን ያገለለውንና በዛሬው እለት በሳኡዲ አረቢያ የሚጀመረውን ንግግር ካመቻቹ በኋላ ነው።
ማክሮን፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስትራመር፣የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ፣ የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክና የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በስብሰባው ከተሳተፉት መሪዎች ውስጥ ይገኙበታል።
ከመሪዎች በተጨማሪ የኔቶ አለቃ ማርክ ሩቴ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዘደንት ኡርዙላ ቭን ደር ሊየንና የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝደንት አንቶኒዮ ኮስታ በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።
ሮይተርስ ያናገራቸው ባለስልጣን እንደገለጹት "ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር በጥንካሬ ላይ የተመሰረተ ሰላም እንዲኖር ተስማምተናል" ብለዋል።
ባለስልጣኑ መሪዎቹ የሰላም ስምምነት ሳይደረስ የሚደረግ ተኩስ አቁም አደገኛ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
የአሜሪካና የሩሲያ ባለስልጣን በዩክሬን ጉዳይ የሚያደርጉት የመጀመሪያው ስብሰባው በዛሬው እለት በሳኡዲ አረቢያ እንደሚጀመር ይጠበቃል።
በዚህ ንግግር ላይ ባለጉዳያዋ ዩክሬንና አውሮፓውያን አይሳተፉም ተብሏል።