“አውሮፓውያን የዩክሬን ጦርነት እንዲቀጥል የሚደግፉ ከሆነ በሰላም ድርድሩ ላይ ለመሳተፍ ለምን ፈለጉ?”-ሰርጌ ላቭሮቭ
የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ውይይት በነገው ዕለት በሳኡዲ አረቢያ ይጀመራል

በዩክሬን የሰላም ድርድር እንደተገለሉ የሚናገሩት የአውሮፓ ሀገራት ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የዩክሬን እና የሩስያ ጦርነት እንዲቀጥል የሚፈልጉ የአውሮፓ ሀገራት በሰላም ድርድሩ ላይ ለመሳተፍ ለምን ፈለጉ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው እና የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ከሩስያ ልኡካን ጋር በነገው ዕለት በሳኡዲ አረብያ በሚካሄደው የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም ውይይት ላይ ለመሳተፍ ሪያድ ገብተዋል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን እና የክሪምሊን አማካሪን በድርድሩ እንዲሳተፉ እንደምትልክ አስታውቃለች፡፡
ከአመታት በኋላ በሞስኮ እና በዋሽንግተን ባለስልጣናት በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ ፊትለፊት በሚደረገው ውይይት ልዑካኑ የሀገራቱ መሪዎች ከመገናኘታቸው በፊት በድርድር ነጥቦች ዙሪያ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከዚህ ባለፈም የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ በተካረረ ሁኔታ ላይ የሚገኘውን የሞስኮ እና የዋሽንግተን ግንኙነት ለማሻሻል ልኡካኑ ይነጋገራሉ፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ በትራምፕ አስተዳደር ገለል የተደረጉት በጦርነቱ ዋነኛ የዩክሬን አጋር እና የጦር መሳሪያ ደጋፊ የነበሩ አውሮፓውያን ሀገራት ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የአውሮፓውን በድርድሩ ካልተሳተፍን ጥያቄን አጣጥለዋል፡፡
አውሮፓውያን ለሶስት አመት ገደማ የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም በርካታ እድል እንደነበራቸው የጠቀሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ሀገራት በድርድሩ ላይ ቢሳተፉም የጎላ አስተዋጽኦ እንደማይኖራቸው ነው የተናገሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት በተባበሩት አረብኤሜሬትስ በጉብኝት ላይ የሚገኙት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ከነገው ውይይት “ፍሬያማ ውጤት” እንደማይጠበቁ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ “ምንም አይነት የዩክሬን ባለስልጣናት ባልተገኙበት ጦርነቱን ስለማስቆም የሚደረግ የትኛውም ውይይት ውጤት አልባ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ወደ ቱርክ የሚያቀኑት ፕሬዝዳንቱ ከነገ ብስቲያ ድግሞ ወደ ሳኡዲ እንደሚያመሩ ተናግረው ጉዟቸው ከሰላም ድርድሩ ጋር እንደማይገናኝ አመላክተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ የዩክሬን ሩሲያ ፖሊሲ ዙሪያ ለመምከር በዛሬው ዕለት በፓሪስ አስቸኳይ ጉባኤ የሚያካሄዱ የአውሮፓ ሀገራት ትራምፕ ጀርባቸውን እንደሰጧቸው እየተዘገበ ነው፡፡
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር “ከፍተኛ የደህንነት ስጋት አንዣቦብናል” ያሉ ሲሆን፤ አውሮፓውን ሀገራት በዩክሬን የሰላም ስምምነትን ተከትሎ የሚደርስባቸውን የደህንነት ስጋት ለመቋቋም አንድ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የፖላንድ፣ ጀርመን፣ፈረንሳይ፣ብሪታንያ እና ሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች እንደሚሳተፉ ሲገለጽ፤ በዋናነት ሩስያ ዳግም በሌላ የአውሮፓ ሀገር ላይ ጥቃት እንዳትከፍት የደህንነት ማስተማመኛ ላይ እንደሚነጋገሩ ተዘግቧል፡፡
ከ4800 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚደረጉት ሁለት ወሳኝ ጉባኤዎች ውጤት የቀጣዩን የአውሮፓ ሀገራት ሰላም እና ደህንነት ሁኔታ እንደሚወስኑት ይጠበቃል ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡