በአስቶንቪላ ያልተሳካለት ጄራርድ በስኮትላንድ ከሬንጀርስ ጋር ስኬታማ ጊዜያት ማሳለፉ አይዘነጋም
ከአምስት ወራት በፊት ከአስቶንቪላ ከተባረረ በኋላ ከስራ ውጭ ሆኖ የቆየው እንግሊዛዊው አሰልጣኝ ስቴቨን ጄራርድ የቱርኩ ክለብ ትራብዞስፖር ቀጣይ አሰልጣኝ ለመሆን ንግግር ጀምሯል ተባለ፡፡
ጀራርድ ከክለቡ ተወካዮች ጋር ለመነጋገር ወደ ኢስታንቡል መብረሩንም ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በቱርክ ሱፐር ሊግ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ትራብዞስፖር፤ ባለፈው ሳምንት በኡምራኒዬስፖር ያጋጠመውን የ2 ለ 1 ሽንፈትን ተከትሎ የቀድሞ አሰልጣኙ አብዱላህ አቪቺን አሰናብቷል፡፡
በዚህም ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ ፍለጋ ለገበያ መውጣቱንና ከጄራርድ ጋር ንግግር መጀመሩ ተገልጿል፡፡
ትራብዞንስፖር ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ቢገጥመውም በሶስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ክለብ ጋር ያለው ልዩነት አምስት ነጥብ ብቻ መሆኑ በፍጥነት የማንሰራራት እድል እንዳለው ያሳያል፡፡
ክለቡ በዚህ የውድድር ዘመን ካደረጋቸው 23 የሊግ ጨዋታዎች 11ዱን አሸንፏል።
የቀድሞ የሬንጀርስ አሰልጣኝ ስቴቨን ጄራርድ ክለቡን የሚረከብ ከሆነ ክለቡ ከዚህም በላይ ሊሻሻል ይችላል ተብሏል፡፡
ስቴቨን ጄራርድ በቅርቡ የፖላንድ ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን አድል አግኝቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የቀድሞ የእንግሊዝ አማካኝ የአሰልጣኝነት ህይወቱን የጀመረው የሊቨርፑል ከ18 አመት በታች በማሰልጠን ሲሆን በ2018 ወደ ስኮትላንድ ተጉዞ ከሬንጀርስ ጋር ስኬታማ ጊዜያት አሳልፏል፡፡
ጄራርድ በስኮትላንድ ያሳካውን ስኬት በእንግሊዝ ለመድገም የአስቶንቪላ አሰልጣኝ ሆኖ ቢቀጠርም ክለቡ ባሳየው ደካማ ጉዞ ባሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት ከክለቡ ሊባረር ችሏል፡፡
አስቶንቪላ በጀራርድ ስር ሆኖ ካደረጋቸው 11 የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሁለቱን ብቻ እንደነበር አይዘነጋም፡፡