ኢትዮጵያ የሰሜኑ ጦርነት በስምምነት እንዲቆም ከፍተኛ ሚና የነበራቸውን አካላት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በተካሄደ ስነስርአት አመስግናለች
በፕሪቶሪያ የተደረሰው ስምምነት ላይ ተሳትፎ ላደረጉ አካላት የምስጋና እና የእውቅና ስነስርአት በአዲስ አበባ ተካሂዷል
በስነስርአቱ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ የቀድሞ የናይጀሪያ እና ኬንያ ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ በርካታ የፌደራልና የክልል አመራሮች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ የሰሜኑ ጦርነት በስምምነት እንዲቆም ከፍተኛ ሚና የነበራቸውን አካላት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በተካሄደ ስነስርአት አመስግናለች።
በአደባባይ በተካሄደው ስነስርአት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ የቀድሞ የናይጀሪያ እና ኬንያ ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ በርካታ የፌደራልና የክልል አመራሮች የተገኙ ሲሆን ንግግሮችም ተደርገዋል።
የትግራይ ህዝብ ጦርነት አንገሽግሾታል - ጌታቸው ረዳ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ባደረጉት ንግግር፥ “ልዩነታችንን በሰለጠነ መንገድ መፍታት ሲገባን ጠመንጃ የመነቅነቅ አባዜ መቶሺዎችን አሳጥቶናል” ብለዋል።
“የትግራይ ህዝብ አሁን እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ወደኋላ የሚመልስ ነገር የሚታገስ አይደለም” ያሉት ሮሰ መስተዳደሩ፥ “ከትግራይ ይዤ የመጣሁትም የሰላምና የፍቅር መልዕክት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
የሰላም ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የወሰዳቸውን ድፍረት የተሞላባቸው እርምጃዎች ሳላደንቅ ባልፍ ንፉግነት ነው የሚሆነው”ም ብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደሩ ፥ ከፌደራሉ መንግስት ጋር ተቀራርቦ መስራት መቻሉንና የመተማመን መንፈስም ቀስ በቀስ እያደገ ስለመምጣቱ አንስተዋል።
የትግራይ ክልል ከአማራ እና አፋር ክልሎች ጋር ግንኙነቱን በማደስ ላይ መሆኑንና የሚያቃቅሩ ጉዳዮችም በህግ እና በንግግር ብቻ ሊፈቱ እንደሚገባ ነው ርዕሰ መስተዳደሩ ያሳሰቡት።
“ፖለቲከኞች የሰላም ቋንቋ ማውራት አለብን” ያሉት አቶ ጌታቸው፥ የሰላም ሂደቱ እንዲጸና እንሰራለን ሲሉም ተደምጠዋል።
የፖለቲካ ንግግር በፍጥነት ሊጀመር ይገባል - ኦባሳንጆ
በፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት እንዲደረስ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፥ ሰላም እንዲመጣም ሆነ ዘላቂ እንዲሆን የተቀናቃኝ ሃይሎችን ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነትን የሚከታተለው ቡድን አዎንታዊ ነገሮችን እየተመለከተ መሆኑን ያነሱት ኦባሳንጆ፥ ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶችን ለመጀመር በመንግስት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎችን በበጎ ጎኑ አንስተዋል።
ይሁን እንጂ በጦርነቱ ምክንያት ያልተከፈቱ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ያልተጀመሩ አገልግሎቶን ማስጀመር ይገባል ነው ያሉት።
የደረሰው ሰብአዊም ሆነ ቁሳዊ ውድመት ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስም የመልሶ ግንባታ እና የተፈናቀሉ ወገኖችን የማቋቋም ስራዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“የፖለቲካ ንግግሮች በፍጥነት ሊጀመሩ ይገባል” ያሉት ኦባሳንጆ፥ ኢትዮጵያውያን መጻኢያቸውን እንዲወሰኑ እና በሀገሪቱ ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ንግግር ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ለአፍሪካ ተምሳሌታዊ ነው - ኬንያታ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በበኩላቸው፥ አፍሪካን የተኩስ ድምጽ የማይሰማባት እና የፖለቲካ ልዩነቶችም በንግግር ብቻ እንዲፈቱ ለማድረግ ህብረቱ ለያዘው ግብ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
ስምምነቱ እውን እንዲሆን ንግግሮቹን ያስተናገዱትን ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ጨምሮ በታዛቢነት የተሳተፉትን አለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የህውሃት ተወካዮች በሰላም ንግግሩ ወቅት ያሳዩትን አብሮነት እና ግልጽ ውይይት በስምምነቱ ተፈጻሚነት ላይ እያሳዩ መሆኑን በማንሳትም ዘላቂ እንዲያደርጉት ጠይቀዋል።
የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ባደረጉት ንግግርም፥ “ኢትዮጵያ በአንድ ባንዲራ ውስጥ በልዩነት መኖር እንደሚቻል ለአፍሪካ ያሳየች ሀገር ናት” ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተደርሰው የሰላም ስምምነት አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላት ያሳየ መሆኑንም በማከል።
በሰላም እጦት ውስጥ ያሉ ሀገራት ኢትዮጵያን ይመለከቱ ዘንድና ከአፍሪካ ህብረት መራሹ ሂደት እንዲማሩም ነው ኬንያታ የጠየቁት።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮነን ባደረጉት ንግግር የሰሜኑን ጦርነት ለማቆም የተደረሰው ስምምነት እንዲጸና ስምምነቱ ሳይሸራረፍ ይተገበራል ብለዋል።
በጦርነቱ በተለያየ ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትንም በሽግግር ፍትህ ለህግ እናቀርባለን ነው ያሉት።
የሰላም ስምምነቱ እንዲፈረምና እንዲጸና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት እና ሀገራት ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።