በደቡብ አፍሪካ በተደረገው ድርድር ሁለቱ አካላት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል
ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፌደራል መንግስት ጋር ጦርነት ገጥሞ የነበረው ህወሓት ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን የኢትዮጵያ ተደራዳሪ አምባሳር ሬድዋን ሁሴን ከስምምነቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል፡፡
ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሀገር ሙከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ነበር በኢትዮጵያ ጦርነት የተጀመረው።
ለሶስት ዙር በድጋሚ በተቀሰቀሰው ጦርነት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን አስከትሏል፡፤
ይህን ጦርነት ለማስቆም የአፍሪካ ህብረት ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተው ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ መዲና የተደረገው ድርድር ዛሬ ተጠናቋል።
የድርድርን መጠናቀቅ ተከትሎ የፌደራል መንግሥትን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ህወሓት ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት የደረሱበትን ስምምነት ለኢትዮጵያውያን እና ለመላው ዓለም የሚጠቅም ነውም ብለዋል።
የህወሃትን ቡድን ልኡክ የመሩት አቶ ጌታቸው ረዳም ባደረጉት ንግግር፥ ስምምነቱን የአዲስ ነገ ጅማሬ ነው ብለውታል።
ህወሓትም ስምምነቱ ለትግራይ እና ለኢትዮጵያ ትልቅ ብስራት ነው ብሏል፡፡
የህወሃትን ቡድን ልኡክ የመሩት አቶ ጌታቸው ረዳም ባደረጉት ንግግር ስምምነቱን የአዲስ ነገር ጅማሬ ነው ብለውታል።
አቶ ጌታቸው ይሁን እንጂ ሁለቱም የስምምነቱ ፈራሚዎች ስምምነቱን አክብረው ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሁለቱ አካላት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባደረጉት ድርድር ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል የህወሀት ትጥቅ መፍታት እና በትግራይ ክልል የሚደረጉ ቀጣይ ስራዎች ናቸው።
ከስምምነቶቹ መካከልም በኢትዮጵያ አንድ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ብቻ እንዲኖር፣ ህወሓት ትጥቅ እንዲፈታ፣ ጦርነቱን በዘላቂነት ማቆም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንዲደረግ እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለዜጎች ማድረስ ዋነኞቹ ናቸው።