ጋና ከአሜሪካ ዶላር ይልቅ ነዳጅ በወርቅ ለመግዛት ማቀዷን ገለጸች
ሀገሪቱ የገጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ያስከተለው የኑሮ ውድነት ለአዲሱ ፖሊሲ መነደፍ በምክንያት ተጠቅሷል
ጋና ድፍድፍ ነዳጅ የምታመርት ቢሆንም በፈረንጆቹ በ2017 በተከሰተ ፍንዳታ ብቸኛው የነዳጅ ማጣሪያዋ ተዘግቷል
የጋና መንግስት የነዳጅ ምርቶችን ከዶላር ይልቅ በወርቅ ለመግዛት አዲስ ፖሊሲ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ም/ፕሬዝዳንት ማሃሙዱ ባውሚያ ተናግረዋል።
እርምጃው እየቀነሰ የመጣውን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከነዳጅ አስመጪዎች የዶላር ፍላጐት ጋር ተዳምሮ ያስከተለውን የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ ያለመ ነው ተብሏል።
የጋና ጠቅላላ የውጭ ምንዛሬ ተቀማጭ በመስከረም 2022 መጨረሻ ላይ ስድስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ላይ ቆሞ የነበረ ሲሆን ይህም ከሦስት ወር ያነሰ የውጭ ንግድ ሽፋን ጋር እኩል ነው ተብሏል። ክምችቱ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ ዘጠኝ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ከነበረው ዝቅ ማለቱን የጋና መንግስት አስታውቋል።
በሚቀጥለው ዓመት አዲሱ ፖሊሲ ገቢራዊ ሲሆን "የክፍያ ሚዛናችንን በመሰረታዊነት ይለውጣል እና የገንዘባችንን የማያቋርጥ የዋጋ ቅነሳን በእጅጉ ይቀንሳል" ብለዋል ባውሚያ።
ፖሊሲው ሻጮች የነዳጅ ምርቶችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ስለማያገኙ የምንዛሪ ዋጋው በቀጥታ በነዳጅ ወይም በፍጆታ ዋጋ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር ያደርገዋል ሲሉም አስረድተዋል።
"በወርቅ የሚሸመት ነዳጅ ትልቅ መዋቅራዊ ለውጥን ያሳያል" ሲሉም አክለዋል።
የታቀደው ፖሊሲ ያልተለመደ ነው ያለው የሮይተርስ ዘገባ፤ ሀገራት አንዳንድ ጊዜ ነዳጅን በሌሎች እቃዎች ወይም ሸቀጦች እንደሚቀያየሩ ጠቅሷል። ነገር ግን ነዳጅ አምራች ሀገር ይህን አማራጭ ማስቀመጧ እንግዳ ሆኗል ብሏል።
ጋና ድፍድፍ ነዳጅ የምታመርት ቢሆንም እ.አ.አ በ2017 ፍንዳታ ከተፈጠረ በኋላ ብቸኛው የነዳጅ ማጣሪያዋ ተዘግቷል። ይህም የተጣራ የነዳጅ ምርቶችን ከውጭ በማስገባት ጥገኛ ሆናለች ነው የተባለው።
የም/ፕሬዝዳንቱ መግለጫ የተሰማው የሀገሪቱ ገንዘብ ሚንስቴር እየተባባሰ ያለውን የእዳ ቀውስ ለመቅረፍ፤ ወጪን ለመቀነስ እና ገቢን ለማሳደግ እርምጃዎችን ማወጃቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።
ካካዋ፣ ወርቅ እና ነዳጅ አምራች የሆነችው ጋና እጅግ የከፋ የምጣኔ-ሀብት ቀውስ እያጋጠማት በመሆኑ መንግስት የእርዳታ ማዕቀፍ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለማግኘት እየተደራደረ ነው።