ተቺዎች ትእዛዙ ህገ መንግስታዊ የእምነት ነጻነት መብትን የሚጋፋ በመሆኑ ህገወጥ ነው ብለውታል
ጋና ፓስተሮቿ አስጨናቂ ትንቢቶችን እንዳይናገሩ አስጠነቀቀች።
የእምነት መሪዎች ፍርሃትን እና ሞትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ባህላዊ የአዲስ ዓመት ትንቢቶችን እንዳይናገሩ የጋና ፖሊስ አስጠንቅቋል።
በጋና ብዙ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ፓስተሮች ስለ አዲሱ ዓመት ትንቢት ሲናገሩ ለመስማት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሰበሰቡ ማየት የተለመደ ነው።
በዚህ ወቅትም ታዲያ የእምነት መሪዎች አስደሳች ከሚመስሉ እስከ ተስፋ አስቆራጭ የሚባሉ ትንቢቶች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
በተለይም ባለፈው ዓመት ህዝቡ በሞት እና በአደጋ ትንበያ ለከፍተኛ ጭንቀት ተዳርጎ እንደነበር የጋናው የዜና ጣቢያ ማይ ጆይ ኦንላይን ዘግቧል።
ይህ ሁኔታ በአሁኑ አዲስ ዓመት እንዳይደገም ያሰጋው የሀገሪቱ ፖሊስ፤ የእምነት መሪዎች ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ትንቢቶች እንዳይናገሩ አስጠንቅቋል፡፡
ተቺዎች ትእዛዙ ህገ መንግስታዊ የእምነት ነጻነት መብትን የሚጋፋ በመሆኑ ህገወጥ ነው እያሉ ነው፡፡
ፖሊስ በበኩሉ የአምልኮ ነጻነት መብት የሌሎችን መብት መጣስ የለበትም ሲል ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡
ፖሊስ በመግለጫው የሃይማኖት ቡድኖች "በህጋዊ መንገድ ተቀባይነት ያላቸውን ትንቢቶች ለመለዋወጥ" ላደረጉት ትብብር አመስግኗል።
የጋና ጠበቃ ሳሚ ዳርኮ ግን የፖሊስ ትዕዛዝ "ህገ-ወጥ ነው" ብለውታል።
"በጋና ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለክርክርም ሆነ ለትርጓሜ እንኳን አይሆንም። በጋና ውስጥ ምንም አይነት ህግ ለፖሊስ አስተዳደር በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ትንቢቶች የመቆጣጠር ስልጣን አይሰጥም" ሲሉም ጽፈዋል ጠበቃው።
ጠበቃው "በምኩራብ፣ በቤተክርስቲያን ወይም በመስጊድ ከሚገኘው 'የአምልኮ ነጻነት' የሃይማኖት ነፃነት ይበልጣል። ይህ ማለት አንድን የተለየ ህግ እስካልጣሰ ድረስ ሰዎች ከባህል ወይም ከመንግስት ጋር ለመስማማት ከዋናው እሴቶቻቸው እና እምነታቸው ጋር መጣጣም የለባቸውም ማለት ነው ” ሲሉም አክለዋል።