የ1 አመት ከ5 ወሩ ጋናዊ ህጻን የአለም በእድሜ ትንሹ ሰአሊ በመሆን ክብረወሰን ያዘ
ከ6ወሩ አንስቶ ከቀለም እና ብሩሽ ጋር የተዋወቀው ጋናዊ የአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ተመዝገቧል
ህጻኑ ሰአሊ የስዕል አውደርዕይ አዘጋጅቶ ስዕሎቹን መሸጥ ችሏል
ሊያም አንክራህ የተባለው ታዳጊ በጋና ዋና ከተማ አክራ ነዋሪ ነው፡፡ ወላጅ እናቱ ቻንትሌ ኩኩዋ ኤግሃን ሰአሊ እና ‘’አርትስ ኤንድ ኮክቴል’’ የተባለ የስዕል ስቱድዮ ባለቤት ነች፡፡
ልጇ ሊያም የስዕል ተሰጥኦ እንዳለው የተረዳችበትን ሁኔታ ስታስረዳ፤ ገና የ6 ወር ጨቅላ እያለ የስዕል ስራዎቿ ላይ ለማተኮር በሚል ጨርቅ ዘርግታ በቀለም እንዲጫወት ሰጠችው፤ ከዛም በእጆቹ መዳፎች የፈጠራቸው መስመሮች የተጠቀማቸው የቀለም ውህደቶች የስዕል ችሎታ ሊኖረው እንደሚችል እንድታሰብ እንዳደረጋት ትናገራለች፡፡
ይህን የመጀመርያ የሊያም ስዕል ‘’ክሮውል’’ ወይም ‘’መዳህ’’ የሚል ስያሜ ወጥቶለት በስዕል ስቱድዮዋ ውስጥ ይገኛል ብላለች::
ከዚህ ግዜ ጀምሮ ሊያም ቀለም እና የስዕል ጨርቅ አልተለያዩም የምትለው እናቱ ኤግሀን አንዳንድ ግዜ እንደ ልጅ ምንም ትኩረቱን ሳይሰርቀው ለሰአታት ያለድካም ቁጭ ብሎ ስዕሎችን እንደሚስል ነው የገለጸችው፡፡
ኤግሀን ልጇ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሙ እንዲሰፍር በባለፈው አመት ሰኔ ላይ ነበር ማመልከቻ ያስገባችው፡፡ በተያዘው አመት ህዳር ወር ላይ ከድርጅቱ ባገኝችው ምላሽ ሊያም የሪከርዱ ባለቤት ይሆን ዘንድ የስዕል ኤግዝቢሽን ማዘጋጀት እና መሸጥ እንዳለበት ትረዳለች፡፡
ከዚህ በኋለ ሊያም ለኤግዝቢሽን የሚሆኑ ስዕሎችን እንዲያዘጋጅ ስትረዳው የነበረችው እናቱ በመጨረሻም ታዳጊው ሊያም በቅርቡ 10 ስሎችን ለእይታ አብቅቶ ዘጠኙን መሸጥ ችሏል፡፡
ይህን ተከትሎም የአለም የድንቃ ድንቅ መዘግብ የአንድ አመት ከአምስት ወሩን ህጻን በእድሜ ትንሹ ወንድ ሰአሊ ሲል ስሙን መዝግቦታል፡፡
ከዚህ ቀደም በእድሜ ትንሽ የሰአሊነት ሪከርድን ይዛ የቆየችው የ11 ወሯ ህንዳዊት አሩሺ ባታንጋር ስትሆን የመጀመርያ ስዕሏን በ60 ዶላር በመሸጥ ሪክዱን ይዛ ትገኛለች። ጋናዊው ሊያም ደግሞ በእድሜ ትንሹ ወንድ ሰዐሊ በመባል ሪከርዱን ተጋርቷታል