ስኳር መጠቀም ብናቆም በቀናት ውስጥ ምን ልዩነት እናያለን?
በምግቦች ወይም በመጠጦች ውስጥ የሚጨመር ስኳርን ማቆም ቆዳን ከማስዋብ እስከ ማስታወስ ችሎታን ማዳበር በርካታ የጤና ጥቅሞች አሉት ተብሏል
ከፍራፍሬዎች የሚገኘው ስኳር ግን ለጤናችን ወሳኝ መሆኑ ሊዘነጋ እንደማይገባው ባለሙያዎች አሳስበዋል
አብዛኞቻችን ስኳርን አብዝቶ መጠቀም ከልክ ላለፈ ውፍረት፣ ለታይፕ 2 ስኳር ህመም፣ ለልብ እና ካንሰር በሽታዎች ተጋላጭነትን ከፍ እንደሚያደርግ እናውቃለን።
ይሁን እንጂ በምግቦች እና መጠጦች ውስጥ የሚጨመረውን ጣፋጭ ነገር መጠቀም ማቆም ወይም መቀነስ ይከብደናል።
የስኳር ፍጆታን መቀነስ ብዛቱ የሚያስከትለውን የጤና እክለ ከማስወገድ ባሻገር የተለያዩ ጥቅሞች እንዳሉት ጥናቶች ያመላክታሉ።
በአሜሪካ ዳላስ የሚኖሩት የስነምግብ ባለሙያ ኤሚ ጎድሰን ስኳርን መጠቀም ማቆም "ለቆዳ ጤና፣ ለጥርስ ንጽህና፣ ለማስታወስ ችሎታ እና የተነቃቃ መንፈስን ለመላበስ ፋይዳው የላቀ ነው" ይላሉ።
ሰዎች እንዴት እነዚህን ጥቅሞች ማግኘት ይችላሉ? የትኞቹ የስኳር አይነቶች ይበልጥ አሳሳቢ ናቸው? እንዴትስ የስኳር ፍጆታን መቀነስና ማቆም ይቻላል? የሚለውንም በዝርዝር ያብራራሉ።
የትኞቹ የስኳር አይነቶች ለጤናችን ጎጂ ናቸው?
የመጀመሪያው መገንዘብ ያለብን ጉዳይ ሁሉም ስኳር ለጤና ጎጂ አለመሆኑን ነው። ተፈጥሯዊ ስኳር እና "የሚጨመር ስኳር" ልዩነትን ማወቅ ይኖርብናል።
በዳቦ ውስጥ የሚገኘው ግሉኮስ፣ በፍራፍሬዎች እና አትክልቶች ውስጥ ያለው ፍሩክቶስ እና ከወተት የምናገኘው ላክቶስ ተፈጥሯዊ ስኳር ናቸው። በቫይታሚን እና ማዕድናት የበለጸጉ ስለሆኑ ከማጣፈጥ እና ሃይል ከመስጠት ያለፈ በርካታ ጥቅሞች አሏቸው።
ለአብነትም ማንጎ ከየትኛውም ፍራፍሬ የበለጠ የተፈጥሯዊ ስኳር ይዘት አለው፤ መካከለኛ መጠን ካለው ማንጎ 20 ግራም ስኳር ይገኛል። ማንጎ ከስኳር ይዘቱ ባሻገር በፕሮቲን፣ ካልሺየም፣ አይረን፣ ማግኒዥየም፣ ፖታሲየም፣ ቫይታሚን ሲ እና በፋይበር የበለጸገ ነው።
እንደ ማንጎ አይነት ፍራፍሬዎችን መመገብ ተፈጥሯዊ ስኳርን ከማግኘት በዘለለ በደም ውስጥ የስኳር መጠን እንዳይበልጥ የሚያግዙ ንጥረነገሮን ያስገኛል ይላሉ በቱፍትስ ዩኒቨርሲቲ የስነምግብ ተመራማሪ የሆኑት አሊስ ሊቸተንስታይን።
በአንጻሩ መጠጦች እና ምግቦች ላይ የሚጨመረው ስኳር በቀን ውስጥ ከ50 ግራም ከበለጠ ለበርካታ የጤና ችግሮች እንደሚዳርግ የአሜሪካ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ይገልጻል።
ምግብን ለማጠፈጥ እና ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ በታሸጉ ምግቦች ላይ የሚጨመሩ ከ260 በላይ አይነት የስኳር አይነቶች እንደ ተፈጥሯዊው ስኳር ቫይታሚን፣ ማዕድናት እና የፋይበር ይዘት የሌላቸው ናቸው። ለዚህም ነው የሚጨመር ስኳር "ባዶ ካሎሪ" ነው የሚባለው።
እነዚህን ስኳሮች ከመጠን በላይ መመገብ ወይም በፈሳሽ መልክ መውሰድ የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅም በማዳከም ለበሽታ ተጋላጭነትን ይጨምራል። ለከፍተኛ የደም ግፊት እና ከደርዘን በላይ ለሚሆኑ የካንሰር አይነቶች ያጋልጣል።
በ2023 የተደረገው የቢኤምሲ ሜዲካል ጥናት 5 በመቶ የስኳር ፍጆታን ማሳደግ የልብ ህመምን ተጋላጭነት በ6 በመቶ ከፍ እንደሚያደርግ አመላክቷል። በተመሳሳይ ለስትሮክ የመጋለጥ እድልን በ10 በመቶ ይጨምራል ብሏል ጥናቱ።
የሚጨመር ስኳር ሰውነታችን ሃይል እንዲያመነጭ አያግዝም፤ እናም በስብ መልክ ይከማቻል የሚለው ጥናቱ፥ ይህም ከልክ ላለፈ ውፍረት እና ተያያዥ የጤና ችግሮች እንደሚዳርግ አብራርቷል።
ምግብና መጠጦች ላይ የሚጨመሩ ስኳሮችን በብዛት መጠቀም ያለእድሜ የሚያስረጁ "ኤጂኢኤስ" የተባሉ ጎጂ ሞሎኪዩሎች እንዲፈጠሩ እና ስር ለሰደደ የመርሳት ችግር ያጋልጣል ተብሏል።
በመሆኑም የደም የስኳር መጠንን እንዳይረጋጋ በማድረግ እንቅልፍ የሚያሳጣውን "የሚጨመር ስኳር" በመቀነስ አልያም በመተው ጤናን ማስተካከል ይቻላል ነው የሚሉት ተመራማሪዎች።
በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰሩ ዋልተር ዊሌት "ስኳር መጠቀም ማቆም በወራትና በአመታት ሳይሆን በቀናት እና በሳምንታት ውስጥ ለውጥ ያሳያል" ባይ ናቸው።
የሚጨመረውን ስኳር መጠቀም ስናቆም ለውጡን ማየት እንጀምራለን የሚሉት ተመራማሪው፥ ከፍራፍሬዎች የምናገኘውን ስኳር ግን መዘንጋት እንደሌለብን ያሳስባሉ።