የሩሲያ ሳይንቲስቶች ስኳርን የሚተካ ምርት ማምረታቸውን ገለጹ
አዲሱ ስኳር በደም ውስጥ ያለውን ስኳር ከፍ አያደርግም ተብሏል
ጣፋጩ ምርት ከካርቦሀይድሬት ይልቅ ፕሮቲን ይዘት እንዳለው ተገልጿል
የሩሲያ ሳይንቲስቶች ስኳርን የሚተካ ምርት ማምረታቸውን ገለጹ፡፡
በየዕለቱ ከተለያዩ ምርቶች ጋር የምንወስደው ስኳር ለውስብስብ የጤና ችግሮች በመዳረግ ላይ ሲሆን በየዓመቱ በስኳር እና ተያያዥ ህመሞች ምክንያት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡
በስኳር ምክንያት በርካቶች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን የሩሲያ ተመራማሪዎች ስኳርን መተካት የሚያስችል አዲስ ምርት ማምረታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሩሲያ ምግብ ፋብሪካ በስኳር ምርት ውስጥ የካርቦሀይድሬት ይዘት የሌለው እና በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን የማይጨምር ምርት ማምረታቸውን አስታውቋል፡፡
ቀይ ስጋ አብዝቶ መመገብ ለስኳር ህመም እንደሚዳርግ ተመራማሪዎች ገለጹ
የምግብ ፋብሪካው ሃላፊ የሆኑት ሮሰቲስላቭ ኮቫሌቭስኪ ለስፑትኒክ እንዳሉት ስኳርን የሚተካ የፕሮቲን ይዘት ያለው ምርት ፈብርከናል ብለዋል፡፡
ይህ ስኳርን ይተካል የተባለው ምርት እንዴት ወደ ተጠቃሚዎች እና ወደ ገበያ እንደሚቀርብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ይህ ምርት በቤተ ሙከራ ይመረታል መባሉ የመሸጫ ዋጋው ውድ ሊሆን እንደሚችል የተሰጋ ሲሆን ከፍራፍሬ እና ፕሮቲን ይሰራልም ተብሏል፡፡
በምርቱ ላይ በተደረገ የመጨረሻ ሙከራ የምርቱ የመጣፈጥ መጠኑ ከስኳር ጋር ሲነጻጸር 10 ሺህ ጊዜ ብልጫ አለውም ተብሏል፡፡
የአዲሱ ስኳር አንድ ግራም ከ10 ኪሎ ግራም ነባሩ ስኳር ጋር ተመሳሳይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የስኳር ምርት ከ2 ሺህ ዓመት በፊት በህንድ እንደተፈበረከ የታሪክ ድርሳናት የሚያሰስረዱ ሲሆን አሁን ላይ ከ420 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በስኳር ህመም ተጠቅተዋል፡፡