የስኮትላንዷ ግላስጎው ነዋሪዎች በአይጦች በሚደርስባቸው ጥቃት መቸገራው ተነገረ
እስካሁን 100 የሚጠጉ ሰዎች በእጅና እግራቸው ላይ በአይጦች በደረሰባቸው ንክሻ በሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ነው
ከእነዚህ አይጦች መካከል አንዳንዶቹ የኩላሊት እና የጉበት ስራ ማቆምን ሊያስከትል የሚችል ባክቴሪያ ተሸካሚዎች ናቸው ተብሏል
በስኮትላንድ የግላስጎው ከተማ ነዋሪዎች በትልልቅ የአይጥ ቡድኖች ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡
እንደ ሚረር ጋዜጣ ዘገባ የአይጦች ጥቃት እና ቁጥር መጨመር በዋና ዋና የግላስጎው ሆስፒታሎች እርዳታ የሚሹ ሰዎችን ቁጥር አሳድጎታል፡፡
የሀገሪቱ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) አሀዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በእጅ እና በእግር ጣቶች እንዲሁም በፊት ላይ ተደጋግሞ በተፈጸመ ጥቃት 98 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በአጠቃላይ ከ100 በላይ ሰዎች በተመሳሳይ ጉዳት በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡
ከ2019 እስከ 2023 ባሉት አመታት በመኖሪያ ቤቶች እና በተለያዩ አካባቢዎች በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የሚደርሱ የአይጥ ጥቃቶች አሻቅበዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማዋ የአይጦች ቁጥር በ45 በመቶ ሲጨምር በመኖሪያ ቤቶች የሚገኙ የአይጦች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
በአይጦች ንክሻ በሚፈጠር ቁስለት “ሴሉላይትስ” የተባለው (የእጅ እና የእግር ጣቶችን የሚያጠቃ ኢንፌክሽን) እንዲሁም በአንጀት ላይ የሚከሰት ባክቴሪያን ጨምሮ ለአረጋውያን እና ለህጻናት አደጋኛ የሆኑ በሽታዎች መበራከታቸው አስጊ መሆኑን ጋዜጣው አመልክቷል።
በምዕራቡ አለም የመከሰት እድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም አንዳንዶቹ አይጦች የኩላሊት እና የጉበት ስራ ማቆምን ሊያስከትሉ የሚችሉ ወይም ከባድ የአተነፋፈስ ችግርን ሊፈጥሩ የሚችሉ ባክቴሪያዎች ተሸካሚዎች ናቸው ተብሏል፡፡
የስኮትላንድ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት አይጦች ከንክሻቸው በተጨማሪ በሽንታቸው፣ በጸጉራቸው ፣ እና ምራቃቸው ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሰዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በርካታ ገዳይ በሽታዎችን ወደ ሰዎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ ሲል አስጠንቅቋል፡፡
መንግስት ይህን ችግር ለመቋቋም ከተለያዩ የጸረ ነብሳት እና የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመወያየት ላይ ሲሆን ዘላቂ መፍትሄው ግን የዜጎችን የህይወት ደረጃ ማሻሻል እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡
በቅርቡ በአይጦች ቁጥር መጨመር የተማረረችው የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ የአይጦችን ስርጭት ለመከላከል የአይጥ የወሊድ መከላከያ ለመስጠት ስለማቀዷ መዘገቡ ይታወሳል፡፡