ኒዮርክ ከተማ የአይጦችን እርባታ ለመከላከል የወሊድ መከላከያ ልትሰጥ መሆኗን ገለጸች
በአሜሪካዋ ኒዮርክ ግዛት የአይጦች መብዛት ነዋሪዎችን እና ተቋማትን አስጨንቋል
በነዋሪዎች ላይ ስጋት የደቀኑት እነዚህ አይጦች በምን መንገድ ይወገዱ የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል
ኒዮርክ ለአይጦች የወሊድ መከላከያ ልትሰጥ መሆኗን ገለጸች።
የዓለማችን ዋነኛ የዲፕሎማት መቀመጫ በሆነችው ኒዮርክ ሲቲ አይጦች ዋነኛ የነዋሪዎች ስጋት ምንጭ ሆነዋል።
የከተማዋ አስተዳድር ከተለያዩ ተቋማት እና ነዋሪዎች ጋር አይጦቹ በምን መንገድ ይወገዱ በሚለው ጉዳይ ዙሪያ በመምከር ላይ ነው።
አይጦቹን ለማስወገድ በመፍትሔነት ከቀረቡት መካከል አይጦቹ ሲንቀሳቀሱ አጣብቆ የሚይዛቸው ኬሚካል እንጠቀም፣ የሚረጭ ኬሚካሎችን መጠቀም፣ እንዲሁም በምግባቸው ላይ ገዳይ ንጥረ ነገሮችን እንጠቀም የሚሉ ቀርበዋል።
ይሁንና የእንስሳት መብት ተቆርቋሪዎች እና ፖለቲከኞች አይጦቹን ለማጥፋት የቀረቡት የመፍትሔ እርምጃዎች ትችቶች ቀርቦባቸዋል።
እንደ ኒዮርክፖስት ዘገባ ከሆነ አይጦቹን ለማጥፋት በመፍትሔነት የቀረቡት ሀሳቦች የአይጥ ዝርያዎችን የሚያጠፋ እና ጨካኝነትን የሚያበረታቱ ናቸው የሚል ትችቶች ቀርቦባቸዋል።
እንዲሁም አይጦቹን በዘመቻ መልክ መግደል የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የአየር ብክለት እንዲከሰት እና ሌሎች ስነ ህይወቶች አብረው እንዲጠፉ ምክንያት በመሆኑ ሊቀር ይገባልም ተብሏል።
ተጨማሪ ባለሙያዎች እና የተለያዩ ተቋማት አመራሮችን ባደረጉት ውይይት የአይጦቹን ቁጥር ለመቀነስ እና ለነዋሪዎች ስጋት እንዳይሆኑ እርባታቸውን መገደብ የሚለው መፍትሔ የተሻለ ተቀባይነት ማግኘቱ ተገልጿል።
በዚህም መሰረት አይጦች እንዳይራቡ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ትክክለኛው መፍትሔ ይሆናል የተባለ ሲሆን በተለይም የወንድ አይጦች የዘር ፍሬያቸው ላይ የሆርሞን ለውጥ እንዲፈጠር ማድረግ እና እንዳይዋለዱ ማድረግ በመፍትሔነት ተወስዷል።