የመረጃ ጥሰቶች ዓለምን በየዓመቱ በ10 በመቶ እያደገ ለሚሄድ ከፍተኛ ወጪ እየዳረጓት ነው ተባለ
የጤና ተቋማት በቀዳሚነት የጥሰቱ ገፈት ቀማሾች ናቸው ነው የተባለው
አንድ የመረጃ ጥሰት በአማካይ 4.2 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብን እንደሚጠይቅ አንድ ጥናት አመልክቷል
የአለም አቀፍ የመረጃ ጥሰቶች ወጪ በየዓመቱ በ10 በመቶ ገደማ እየጨመረ መምጣቱን ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ተቋም ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ማሽንስ ኮርፖሬሽን (IBM) አስታወቀ፡፡
IBM ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ በአንድ የመረጃ ጥሰት የሚጠየቀው አማካይ ወጪ ወደ 4.2 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውቋል፡፡
እንደ ተቋሙ ገለጻ የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ ከቤት ሆኖ የመስራት መዘውተሩ እና የቴክኖሎጂ እድገቱ ለመረጃ ጥሰቱ መባባስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡
በዋናነትም የጤና ተቋማት ጥሰቱን ተከትሎ ከፍተኛውን ዋጋ የከፈሉ ተቋማት ናቸው፡፡ ይህ ለተከታታይ 11ኛ ዓመት የሆነ ነው፡፡
ከሰራተኞቻቸው መካከል 50 በመቶ ያህሉ ከስራ ቦታቸው ውጭ ሆነው የሚሰሩ ተቋማት የመረጃ ጥሰቱን የመለየታቸው ነገር 58 በመቶ ያል ብቻ መሆኑንም ነው IBM ያስታወቀው፡፡ ይህም ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ ዋሽንግተን ባደረገው ፔኖሞን ኢንስቲትዩት የተካሄደው የIBM ጥናት ባለፈው ዓመት በተለያዩ 17 ግዛቶች በሚገኙ 17 አምራች ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ተጨባጭ የመረጃ ጥሰቶችን በመተንተን የተካሄደ ነው፡፡
በጥሰቱ ከፍተኛ ዋጋን እየከፈሉ ካሉ ሃገራት መካከል አሜሪካ ቀዳሚዋ ነች፡፡ አሜሪካ በቅርቡ እንኳ በነዳጅ ኩባንያዎቿ በኩል ያጋጠማት የሳይበር ጥቃት የሚታወስ ነው፡፡
ሳዑዲ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችም ይጠቀሳሉ፡፡ ካናዳ፣ ጀርመንና ጃፓንም በጥሰቱ ምክንያት ለከፈተኛ ወጪ ከተዳረጉ ሃገራት መካከል ናቸው፡፡