በአዲሱ 2024 ዓመት የዓለምን ፖለቲካ የሚወስኑ ከ40 በላይ ምርጫዎች ይካሄዳሉ
አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ እስራኤል፣ ታይዋን እና ህንድ ምርጫ ከሚያካሂዱ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው
የታይዋንን ነጻነት የሚደግፈው ፓርቲ ስልጣን ከተቆጣጠረ ቻይና እና አሜሪካ ወደ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ ተብሏል
በአዲሱ 2024 ዓመት የዓለምን ፖለቲካ የሚወስኑ ከ40 በላይ ምርጫዎች ይካሄዳሉ፡፡
ከቀናት በኋላ በሚገባው አዲሱ የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ውስጥ ከ40 በላይ ሀገራት ምርጫ እንደሚደርጉ ተገልጿል፡፡
40 በመቶ የዓለማችን ህዝቦች የሚያስተዳድራቸውን መንግስት ለመወሰን ድምጽ ይሰጣሉ የተባለ ሲሆን አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ኢራን፣ እስራኤል፣ ታይዋን፣ ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎችም ሀገራት ምርጫ ከሚደረግባቸው ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የምርጫዎቹ ውጤት የዓለምን የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ አሰላለፍ ሊቀይሩ ይችላሉ የተባለ ሲሆን የምርጫዎቹ ውጤቶች እና ወደ ስልጣን የሚመጡት ተመራጮች አዳዲ ውሳኔዎችን የሚወስኑ ሊሆኑ ይችላሉም ተብሏል፡፡
ለታይዋን ሙሉ ነጻነት ለማረጋገጥ የሚሰራው ፓርቲ በምርጫው አብላጫ ድምጽ ካገኘ ቻይና ጣልቃ ለመግባት ስትሞክር ከአሜሪካ ጋር ወደ ጦርነት ልትገባ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
ሌላኛው ምርጫ የሚካሄድበት ሀገር እስራኤል ትሆናለች የተባለ ሲሆን በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አመራር ደስተኛ ያልሆኑ ዜጎች መበራከትን ተከትሎ አዲስ መሪ ሊመጣ ይችላል ተብሏል፡፡
ሌላኛዋ ምርጫ የሚደረግባት ሀገር ሩሲያ ስትሆን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአምስተኛ ጊዜ ተወዳድረው ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል፡፡
በጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን የፊታችን መጋቢት ፕሬዝዳንታ ምርጫ ለማካሄድ ፕሮግራም የያዘች ሲሆን አዲስ ፕሬዝዳንት ሊመጣ ይችላል ተብሏል፡፡
አፍሪካዊቷ ደቡብ አፍሪካ የፊታችን ሚያዝያ ወር ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የምታካሂድ ሲሆን ላለፉት 30 ዓመታት ስልጣን በአብላጫ ይዞ የቆየው ኤኤንሲ ፓርቲ ሊሸነፍ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
ግንቦት ላይ ደግሞ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለ ህዝብ ብዛት ባለቤት የሆነችው ሕንድ በታሪክ ግዙፉን ምርጫ እንደምታካሂድ ሲገለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የ28 ፓርቲዎች ጥምረት በሆነው የሕንድ ብሔራዊ ጥምረት ለልማት ፓርቲ የመሸነፍ እድላቸው ሰፊ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሕንድ አዲስ መሪ ወደ ስልጣን የሚመጣ ከሆነ አሜሪካ ቻይናን በእስያ ለመገዳደር በያዘችው እቅድ ላይ እንቅፋት አልያም ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ተብሏል፡፡
የኮሎራዶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ እንዳይፎካከሩ ወሰነ
ሌላኛዋ ምርጫ የምታካሂደው ሀገር ብሪታንያ ስትሆን ያለባትን የጠቅላይ ሚኒስትሮች አለመረጋጋት ምላሽ እንደምትሰጥ ተጠብቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ክሮሺያ እና ፊንላንድ ምርጫ ያካሂዳሉ የተባለ ሲሆን የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ምርጫም ይካሄዳል፡፡
በአውሮፓ የሚደረጉ ምርጫዎች በቀኝ ዘመም ወይም ስደተኞችን የሚጠሉ ፓርቲዎች ስልጣን እየተቆጣጠሩ በመምጣት ላይ ናቸው፡፡
አስቀድማ በሴት ፕሬዝዳንት እንደምትመራ ያረጋገጠችው ሜክሲኮ ሀምሌ ላይ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ሁለት ሴት እጩ ፕሬዝዳንቶች ይወዳደራሉ ተብሏል፡፡
የዓመቱ የመጨረሻ ምርጫ የሚካሄደው በአሜሪካ ሲሆን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ የመጨረሻ እጩ ሆነው እንደሚቀርቡበት ይጠበቃል፡፡