የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ የነበሩት ብርቱካን ሚደቅሳ በራሳቸው ፍላጎት ከኃፊነት መልቀቃቸው ይታወሳል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሹመትን አስጽድቋል።
በዚህም ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አቅራቢነት ወ/ሮ ሜላትወርቀ ኃይሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በማድረግ ሾሟል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሹመቱን በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምመጽ አጽድቋል።
ወ/ሮ ሜላትወርቀ ኃይሉ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ እንደሚገኙ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገልቷል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ሜላትወርቀ ኃይሉ በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ-ማሃላ ፈጽመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ የነበሩት ብርቱካን ሚደቅሳ ከነሀሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ኃላፊነት በራሳቸው ፈቃድ መልቀቃቸው ይታወሳል።
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በ2011 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ ነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በመሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሸመው ስራ የጀመሩት።
በሃላፊነት ላይ በነበሩባቸው 4 ዓመት ከስድስት ወራት አንድ ሀገራዊ ምርጫ እንዲሁም ሶስት ህዝበ ውሳኔዎችን መምራት ችለዋል።
በተያያዘ ዜና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቶ ጌትነት ታደሰን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አድርጎ ሾሟል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ አቶ መሳፍንት ተፈራን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ በማድረግ ሾሟል።