የዓለም ወፍራሞች ቀን አየተከበረ ይገኛል
የውፍረት በሽታ በገዳይነቱ የዓለማችን አራተኛው በሽታ ነው
በዓለማችን ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች በዚህ በሽታ መጠቃታቸውን ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል
የዓለም ወፍራሞች ቀን አየተከበረ ይገኛል፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ አንድ ሰው የቁመቱ እና ክብደቱ አማካኝ 30 እና ከዛ በላይ ከሆነ የውፍረት በሽታ አለበት ይባላል፡፡
እንዲሁም አንድ ሰው የቁመቱ እና ክብደቱ አማካኝ ከ25 እስከ 29 ከሆነ ከመጠን በላይ ክብደት አለበት እንደሚባልም ተገልጿል፡፡
ውፍረት እና ከመጠን በላይ ክብደት ባልተመጣጠነ ምግብ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረግ እና ከመጠን በላይ መመገብ ምክንያቶች ይከሰታል፡፡
በ2035 ግማሹ የዓለም ህዝብ ከልክ ላለፈ ውፍረት ይጋለጣል ተባለ
እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ ውፍረት ወይም ከመጠን በላይ ክብደት ለስኳር፣ ደም ግፊት ፣ ልብ ሕመም፣ ካንሰር እና ሌሎች ተያያዥ ህመሞች ያጋልጣል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ በየዓመቱ መጋቢት 4 ቀን ስለ ውፍረት በሽታ ግንዛቤ በመፍጠር ተከብሮ እንዲውል በወሰነው መሰረት በዛሬው ዕለት እየተከበረ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ ዕለቱን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች ወይም ከስምንት ሰዎች መካከል አንዱ በውፍረት በሽታ መጋለጡን አስታውቋል፡፡
የአመለካከት ችግሮች ሰዎች ለውፍረት የተዛባ አመለካከት እንዲያዙ ማድረጉን የገለጸው ድርጅቱ በተወሰኑ የአፍሪካ እና እስያ ሀገራት ውፍረትን የውበት እና የምቾት መገለጫ አድርጎ የመረዳት አመለካከት መኖሩን አስታውቋል፡፡
የውፍረት በሽታ ከደም ግፊት እና ልብ ሕመም ቀጥሎ ሶስተኛው ዓለማችን ገዳይ በሽታ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በዓለማችን ብዙ ዜጎቻቸው በውፍረት በሽታ ከተጠቁባቸው ሀገራት መካከል ኩዌት፣ አሜሪካ፣ ሊቢያ፣ኳታር እና ባህሬን ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ድረስ ያለውን ደረጃ ሲይዙ ኢትዮጵያ፣ ቬትናም፣ኤርትራ፣ ካምቦዲያ እና ሩዋንዳ ደግሞ ዝቅተኛ የውፍረት በሽታ ተጠቂ ዜጎች ያለባቸው ሀገራት ናቸው፡፡