የኮፕ28 ፕሬዝዳንት በጉባኤው የተሳተፉ 197 ሀገራትን ለተሻለ ውሳኔ ማብቃቱ ተገለጸ
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ሀገራት እና ተቋማት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን ጋዝ መቀነስ አማራጭ የሌለው ብለዋል
በዱባይ እየተካሄደ ያለው የኮፕ28 ጉባኤ 12ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
52 የዓለማችን ነዳጅ አምራች ኩባንያዎች የካርበን ጋዝ ልቀታቸውን ለመቀነስ ተስማሙ፡፡
በአረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የኮፕ28 አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ 12ኛ ቀኑን ይዟል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ጋር በመምከር ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ምድራችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስ ጉዳትን መቀነስ የሚያስችሉ ምክክሮች እና ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡
የአረብ ኢምሬት ኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና የኮፕ28 ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አህመድ አልጃቢር ሀገራት እና ተቋማት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ በካይ ጋዝን መቀነስ አማራጭ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ሱልጣን አክለውም በጉባኤው ላይ ለተሳተፉት አካላት ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራት እና ተቋማት ከግትርነት ወጥተው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትን ለመቀነስ የግድ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው በካጠይ ጋዝ መጠን መቀነስ ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለይም የነዳጅ አምራች ሀገራት እና ኩባንያዎች በካይ ጋዝን ለመቀነስ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመር አለባቸው ያሉ ሲሆን እስካሁን 52 ዓለም አቀፍ የነዳጅ ኩባንያዎች የካርበን ጋዝ ልቀታቸውን ለመቀነስ መስማማታቸው ተገልጿል፡፡
የአየር ንብረት ፕሮጀክቶች ለምን የፋይናንስ እጥረት ያጋጥማቸዋል?
ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን ካርበን ጋዝ ለመቀነስ የተስማሙት ኩባንያዎች ለአየር ንብረት ለውጥ የ40 በመቶ ድርሻ እንዳላቸውም ዶክተር ሱልጣን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ሱልጣን አክለውም የካርበን ጋዝ ልቀታቸውን ለመቀነስ የተስማሙት ኩባንያዎች በቂ አለመሆናቸውን ገልጸው ሌሎች ሀገራት እና ኩባንያዎችም እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዛሬው የኮፕ28 የመዝጊያ ጉባኤ ላይ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወደ ዱባይ ተመልሰው በሚደረጉ ተጨማሪ ድርድሮች ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡