ኮፕ28 ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ አዳዲስ መፍትሄዎችን አመላክቷል - ሲሞን ስቲል
የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን ዋና ጸሃፊው ሀገራት በኮፕ28 የቀረቡ የመፍትሄ አቅታጫዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል
በዱባይ እየተካሄደ የሚገኘው 28ኛው አለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ 10ኛ ቀኑን ይዟል
ኮፕ28 በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በቀጣይ አመታት ለሚካሄዱ ስራዎች መነሻ የሆኑ በርካታ ውሳኔዎች የተላለፉበት መሆኑ ተገልጿል።
የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን ዋና ጸሃፊው ሲሞን ስቲል እንዳስታወቁት፥ የዱባዩ ጉባኤ በመላው አለም በአየር ንብረት ቀውስ እየተፈተኑ ለሚገኙ ሀገራት መፍትሄዎችን አስቀምጧል።
ዋና ጸሃፊው ከኮፕ28 ጉባኤ ጎን ለጎን በሰጡት መግለጫ በኮፕ28 ከአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች መውጫ መንገዶች እና አዳዲስ ስልቶች ተዋውቀዋል ብለዋል።
የሀገራት የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ሚኒስትሮች እንዲሁም ተደራዳሪዎች እነዚህን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ጥቅም ላይ እንዲያውሏቸውም ነው የጠየቁት።
በኮፕ28 የተደረሱ ውሳኔዎች እና የተገቡ የድጋፍ ቃልኪዳኖች በቀጣይ ለሚደረጉ የአየር ንብረት ለውጥ ዘመቻዎች እንደመስፈንጠሪያ መዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የሀገራት መሪዎችም በተለይ ብክለት የሚያስከትሉት በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ለሚደርስባቸው ታዳጊ ሀገራት የሚያደርጉት የፋይናንስ ድጋፍ ይበልጥ ማደግ እንደሚገባውም ነው የተናገሩት።
10ኛ ቀኑን በያዘው የኮፕ28 ጉባኤ ሀገራት ከ83 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተውበታል።