አዲሱ የቴሌኮም ኩባንያ በቀጣዩ የፈረንጆች አመት መጀመሪያ ወደ ስራ እንደሚገባ አስታወቀ
በኩባንያው የታቀደው ኢንቨስትምንት መጠን ከሀገሪቱ የሁለት አመት ኤክስፖርት ገቢ በላይ መሆኑ ነው ተብሏል
ኩባንያው በፈረንጆቹ ከ2022 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ጀምሮ በ10 ዓመት ጊዜ ለመንቀሳቀስ የሚያችለው ከ8.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድቧል
ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የሚሰኘውና ፍቃድ ያገኘው የቴሌኮም አገልሎት ሰጪ ባወጣው መግለጫ በትምህርት: በጤና እና በግብርና ቴሌኮም ለኢትዮጵያ ልዩነት እንደሚያመጣ አስታውቋል፡፡
የቮዳፎን ግሩፕ አባል በሆነው ሳፋሪኮም የሚመራው ይህ ጥምረት በፈረንጆቹ ከ2022 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ጀምሮ በአስር ዓመት ጊዜ ለመንቀሳቀስ የሚያችለው ከ8.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ ፤ የቴሌ ኮምዩኒኬሽን አገልግሎትን በኢትዮጵያ ለመጀመር አቅደዋል፡፡
ኩባንያው የታቀደው ኢንቨስትምንተ መጠን ከሀገሪቱ የሁለት አመት ኤክስፖርት ገቢ በላይ መሆኑ ነው፡፡
ጥምረቱም ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕ፣ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን የተባሉ ግዙፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያዎች እንዲሁም ሲዲሲ ግሩፕ የተሰኘ የዩናይትድ ኪንግደም የልማት ማዋዕለ ነዋይ አቅራቢ ተቋምን ያካትታልም ነው የተባለው፡፡
የሳፋሪኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፒተር ዴግዋ “የቴሌኮም የመገናኛ አውታሮችን በመዘርጋት ዲጂታል የኑሮ ዘይቤን ለማቅረብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መስራት የምንችልበት ዕድል በማግኘታችን እጅግ ደስተኞች ነን” ብሏል፡፡
የቮዳኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ሻሚል ጁሱብ በበኩሉ “ቮዳኮም በፈረንጆቹ በ2025፤ 100 ሚልየን አፍሪካውያንን በቴሌኮም ለማስተሳሰር የገባውን ቃል ለማሳካት መጠነሰፊ የዲጅታል መዕቀፍ ማስፋፍያዎችን” እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
“በዓለም ላይ ለቴሌኮም ገበያ ውድድር በራቸውን ለመክፈት ከመጨረሻዎቹ አገሮች ተርታ ለሆነችው ኢትዮጵያ ይህ ወሳኝ የዕድገት ደረጃ ነው” ብሏል የቮዳፎን ግሩፕ ዋና አስፈጻሚ ኒክ ሪድ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ጨረታ ያሸነፈውን የውጭ ኩባንያ ይፋ ሲያደርጉ፤ የተገኘውን ኢንቨስትመንት “ታሪካዊ ነው” በማለት ገልጸው ነበር፡፡