ተፎካካሪ ስማርት ስልክ አምራቾች በሶስተኛው ሩብ አመት ስንት ስልክ ሸጡ?
ግዙፉ የደቡብ ኮርያ ኩባንያ ሳምሰንግ 19 በመቶ የገበያ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚው ነው
በሩብ አመቱ በአጠቃላይ ከ309.9 ሚሊየን በላይ ስልኮች ተሸጠዋል
ተንቀሳቃሽ ስልኮች (ሞባይል) አሁን አሁን መልዕክት ከመቀያየሬነት አልፈው የሰው ልጅ በዕለት ውሎው በርካታ እንቅስቃሴዎችን የሚከውንባቸው መሳርያዎች ወደ መሆን ተሻግረዋል፡፡
በአምራች ኩባንያዎች መካከል ከፍተኛ የሽያጭ ድርሻን እና ተመራጭነትን ለማግኝት በሚደረገው ፉክክር ሶፍትዌሮችን እና የቴክኖሎጂ ግኝቶችን በመጨመር በየጊዜው አዳዲስ ስማርት ስልኮችን ለገበያ ያቀርባሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የካሜራ ጥራት ፣ የባትሪ ቆይታ እና መረጃ ከመያዝ አቅም ባለፈ የሰውሰራሽ አስተውሎቶች አጠቃቀምን በስልክ ውስጥ በመጨመር የሚደረገው የቴክኖሎጂ እሽቅድድም እያደገ ይገኛል፡፡
በዚህም በየጊዜው አዳዲስ አገልግሎቶችን አካተው የሚቀርቡ ስማርት ስልኮችን ለመሸመት በገዢዎች ዘንድ የምርጫ መደናገር እስከመፍጠር እንደደረሰ ይነገራል፡፡
በስማርት ስልኮች የገበያ ድርሻ እና ደረጃ ዙርያ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያወጣው “ካናሊስ ሪሰርች” ይፋ ባደረገው ሪፖርት የ2024 ሶስተኛ ሩብ አመት ሽያጭ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የአምስት በመቶ ብልጫ እንዳለው አመላክቷል፡፡
በሩብ አመቱ 309.9 ሚሊየን ስልኮች በተለያዩ የአለም ክፍሎች ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አምስት የስማርት ስልክ አምራቾች ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ እንደሚሸፍኑ ተጠቅሷል፡፡
ሳምሰንግ ፣ አፕል ፣ ሻውሚ ፣ ኦፖ እና ቪቮ ገበያውን በቀዳሚነት እየመሩ የሚገኙ አምራቾች ናቸው፡፡
የእስያ ፓስፊክ ቀጠና በስማርት ስልኮች ገበያ እድገት ቀዳሚነቱን ሲይዝ በየአመቱ ያለው የገበያ ድርሻም በ10 በመቶ እያደገ መምጣቱ ነው የተነገረው፡፡
ላቲን አሜሪካ ፣ ቻይና እና አፍሪካ በ9 እና 4 በመቶ የገበያ እድገት በደረጃው በተከታታይነት ይገኛሉ፡፡
በሶስተኛው ሩብ አመት 57.5 ሚሊየን ስልኮችን የሸጠው የደቡብኮርያው ሳምሰንግ ኩባንያ ቀዳሚው ሲሆን በቅርቡ አይፎን 16ትን ያስተዋወቀው የአሜሪካው አፕል በበኩሉ 54.5 ሚሊየን ስልኮችን መሸጥ ችሏል፡፡