ፈረንሳይ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ስፔን፣ ጀርመን እና ሌሎችም ሀገራት የፕሬዝዳንቱን እቅድ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመዋል
የአሜሪው ፕሬዝዳንት ጋዛን በጊዜያዊነት ለመቆጣጠር ያቀረቡት ሀሳብ ከፍተኛ አለምአቀፋዊ ውግዘት ገጥሞታል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በአሜሪካ በጉብኝት ላይ ከሚገኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በዋይት ሃውስ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መገለጫ፤ የጋዛን ፍርስራሾች ለማጽዳት እና የተቀበሩ ቦንቦችን አስወግዶ ድጋሚ ለኑሩ ምቹ ለማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ይህን ሂደት ለማከናወን ፍልስጤማውያን በጎረቤት ሀገራት እንዲሰፍሩ የጠየቁት ትራምፕ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ትራምፕ የጋዛ ሰርጥን ሙሉ ለሙሉ በጊዜያዊነት መቆጣጠር እንደሚፈልጉ ነው የገለጹት፡፡
ይህን ተከትሎ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የፕሬዝዳንቱን ሀሳብ ውድቅ በማድረግ ተቃውሞውን እያሰማ ይገኛል፡፡
ከፍተኛ የሀማስ ባለሥልጣን የሆኑት ሳሚ አቡ ዙህሪ ሀሳቡን ባጣጣሉበት ንግግራቸው “በጋዛ ሰርጥ ያሉ ህዝቦቻችን ይህ እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን አይፈቅዱም፤ ዜጎች የሚፈልጉት የእስራኤል ወረራ እንዲቆም እንጂ ከሀገራቸው ማባረርን አይደለም” ብለዋል፡፡
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ “ፍልስጤማውያን መሬታቸውን፣መብታቸውን እና የተቀደሱ ቦታዎችን አይለቁም። የጋዛ ሰርጥ ከዌስት ባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም ጋር የፍልስጤም ግዛት ዋና አካል ነው በማለት” ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን አስቀድመው ከተቃወሙ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሳኡዲ ልዑል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን ፍልስጤማውያንን ከምድራቸው የማስወጣት የትኛውንም ሙከራ እቃወማለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በበኩላቸው የጋዛ ሰርጥ የፍልስጤማውያን መሆኑን ከስፍራው መፈናቀላቸው ተቀባይነት የሌለው እና ከአለም አቀፍ ህግ ጋር የሚቃረን ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ “ሂደቱ ወደ አዲስ ስቃይ እና አዲስ ጥላቻ ሊያመራ ስለሚችል በፍልስጤማውን ጉዳት ላይ የተመሰረተ ማንኛውም መፍትሄ ሊሰራ አይችልም” በሚል ተቃውመዋል፡፡
የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ”የአካባውን ግጭት ለማስቆም የሁለት ሀገርነት መፍትሄ መተግበር ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ በተደጋጋሚ አቋማችንን ይፋ አድርገናል፤ ፍልስጤማውያን በሀገራቸው፣ በጋዛ፣ በዌስት ባንክ መኖር እና መበልጸግ ሲችሉ ማየት እንሻለን” ነው ያሉት፡፡
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ክሪስቶፍ ሊሞን ፈረንሳይ በጋዛ የፍልስጤም ህዝብ ላይ የሚደረገውን ማንኛውንም የግዳጅ ማፈናቀልን ትቃወማለች ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ ባለፈም ፍልስጤማውያን በሀገርነት በይፋ ለመመስረት ያላቸውን ህጋዊ ምኞት የሚገድል እና በፈረንሳይ አጋሮች ግብፅ እና ዮርዳኖስ እንዲሁም በመላው ቀጠና ትልቅ አለመረጋጋትን እንደሚያስከትል አሳስበዋል፡፡
የጋዛን መልሶ ግንባታ ፍልስጤማውያንን ከቀያቸው ባለፈናቀለ መልኩ የሚደረግ የመልሶ ግንባታን ብቻ እንድመትደግፍ ያሳወቀችው ደግሞ ግብጽ ናት፡፡
የክሪምሊን ቃልአቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “ከአንድ ወገን የመነጨ ከፍልስጤማውን ድጋፍ ያላገኘ የመፍትሄ ሀሳብ መጨረሻው መፍረስ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች መስፈራቸው አስገዳጅ ከሆነ እንኳን የሁለት ሀገርነት መፍትሄ በቅድሚያ ገቢራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ “ቻይና ሁሉም ወገኖች የተኩስ ማቆም እና የድህረ-ግጭት አስተዳደርን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የፍልስጤም ጉዳይ በሁለቱ ሀገራት መፍትሄ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እልባት እንዲያገኝ ትሻለች” ነው ያለችው፡፡
ቱርክ፣ አውስትራሊያ፣ አየርላንድ፣ ኢራን፣ ቱርክ፣ ስፔን እና ሌሎችም የትራምፕን ሀሳብ ተቃውመው መግለጫ ያወጡ ሀገራት ናቸው፡፡