የጄጁ ኤየር አውሮፕላን 'ብላክ ቦክ' መረጃ መመዝገብ ያቆመው ከመከስከሱ ከአራት ደቂቃ በፊት እንደነበር የደቡብ ኮሪያ የትራስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ
አውሮፕላኑ ከመጋጨቱ ከአራት ደቂቃ በፊት የአውሮፕላኑ አብራሪዎች የወፍ ምት እንዳጋጠማቸው እና በድንገት ለማረፍ እንደወሰኑ ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አሳውቀዋል
የድምጽ መቅጃው መጀመሪያ የተመረመረው ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የነበረ ሲሆን መረጃ መጥፋቱ ሲታወቅ ግን ለአሜሪካ ትራስፖርቴሼን ሴፍቲ ቦርድ መላኩን ሚኒስቴሩ ገልጿል
የጄጁ ኤየር አውሮፕላን 'ብላክ ቦክ' መረጃ መመዝገብ ያቆመው ከመከስከሱ ከአራት ደቂቃ በፊት እንደነበር የደቡብ ኮሪያ የትራስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
ከ12 ቀናት በፊት የተከሰከሰው የደቡብ ኮሪያው ጄጁ ኤየር አውሮፕላን የበረራ መረጃ እና የኮክፒት ድምጽ መመዝገቢያ ወይም ብላክ ቦክስ ስራውን ያቆመው አውሮፕላኑ በደቡብ ኮሪያው ሙአን ኤየርፖርት ካለ ኮንክሪት ጋር ከመጋጨቱ ከአራት ደቂቃ በፊት መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስቴሩ በዛሬው እለት አስታውቋል።
የሀገሪቱ ባለስልጣናት በደቡብ ኮሪያ ታሪክ እጅግ ከባድ እና ለ179 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን አደጋ እና ብላክ ቦክሱ ስራውን እንዲያቆም ያደረገው ምን እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ እንደሚገኙ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የድምጽ መቅጃው መጀመሪያ የተመረመረው ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የነበረ ሲሆን መረጃ መጥፋቱ ሲታወቅ ግን ለአሜሪካ ትራስፖርቴሼን ሴፍቲ ቦርድ መላኩን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ ገዳት የደረሰበት የበረራ መረጃ መመዝገቢያ ከአሜሪካ ሴፍቲ ተቆጣጣሪዎች ጋር በትብብር ለመመርመር ወደ አሜሪካ ተልኳል ብሏል።
ከታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ የተነሳው ጄጁ ኤየር 7C2216 ደቡብ ኮሪያ ሙአን ሲደርስ በደረቱ በማረፉ እና ከማኮብኮቢያ መስመር ውጭ በመውጣት ከኮንክሪት ጋር ተጋጭቶ በእሳት ሊያያዝ ችሏል።
አውሮፕላኑ ከመጋጨቱ ከአራት ደቂቃ በፊት የአውሮፕላኑ አብራሪዎች የወፍ ምት እንዳጋጠማቸው እና በድንገት ለማረፍ እንደወሰኑ ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አሳውቀዋል። በአውሮፕላኑ የኋላ ክፍል ላይ የነበሩ ሁለት የበረራ ሰራተኞች በህይወት ተርፈዋል።
የአስቸኳይ መልእክት ከመምጣቱ በፊት ከሁለት ደቂቃ በፊት የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የወፍ ግጭት ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር።
የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የአደጋ መርማሪ ለሮይተርስ እንደተናገሩት የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወሳኝ መረጃ መጥፋቱ መታወቁ የሚገርም እና ያልተለመደ ነው ብለዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሌሎች መረጃዎች በምርመራው ጥቅም ላይ እንደሚውል እና ምርመራው በግልጽነት እንደሚደረግ እና ለተጎጅ ቤተሰቦች እንደሚጋራ ገልጿል።
የተወሰኑ የተጎጂዎች ቤተሰቦች የትራንስፖርት ሚኒስቴር በምርመራው ላይ የመሪነት ሚና ሊኖረው አይገባም የሚል ቅሬታ እያሰሙ ናቸው።