የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያቀኑ ተነገረ
በዲፕሎማሲ ውጥረት ውስጥ የቆዩት ሁለቱ ጎረቤት ሀገራት ከአንካራው የመሪዎች ስምምነት በኋላ ወደ አዲስአበባ እና ሞቃዲሾ ከፍተኛ ልዑካን ቡድናቸውን ልከው ተወያይተዋል
ሀሰን ሼክ ባለፈው አመት የካቲት ወር በ37ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ከተሳተፉ ወዲህ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ በዛሬው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀኑ ተገለጸ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑት የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ግንኙነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ለመምከር መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ፕሬዝዳንት መሀመድ እና ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የአንካራ ስምምነትን ተግባራዊ በማድረግ እና በሶማሊያ አዲሱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የኢትዮጵያን ሚና ጨምሮ በተለያዩ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱም መሪዎች በቀጠናዊ መረጋጋት፣ በኢኮኖሚ ትብብር እና በስትራቴጂያዊ አሰላለፍ ላይ ያላቸውን ትብብር ማሳደግ ይፈልጋሉ።
ይህ ጉብኝት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ እ.ኤ.አ የካቲት 17 ቀን 2023 በ37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከተሳተፉበት ጊዜ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ነው፡፡
በወቅቱ ሀገራቱ ከነበሩበት ውጥረት ጋር በተያያዘ፤ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች የፕሬዝዳንቱን እንቅስቃሴ ለመገደብ ሞክረው ከጅቡቲው ፕሬዝዳንት ጋር ተቀላቅለው ከሆቴላቸው እንዲወጡ ተገደዋል የሚል ውንጀላ የተሰማበት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ለንግድ እና ጦር ሰፈር የሚያገለግል ወደብ ለመከራየት ባለፈው አመት ጥር ወር የመግባብያ ስምምነት መፈጸሟን ተከትሎ ሞቃዲሾ እና አዲስአበባ ከአንድ አመት በላይ በውጥረት ውስጥ እንደቆዩ ይታወሳል፡፡
በቱርክ አደራዳሪነት ሁለቱን ሀገራት ለማሸማገል ሲደረግ የነበረው ጥረት ፍሬ አፍርቶ በታህሳስ 2024 የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በአንካራ ፊትለፊት ተገናኝተው ውጥረቶችን ለማቃለል ተስማተዋል፡፡
ስምምነቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከሶማሊያ የሉዓላዊነት ስጋቶች ጋር በማጣጣም አዲስ አበባ የሶማሊያ ወደቦችን እንድትጠቀም እንደሚያስችል መነገሩ ይታወሳል፡፡
በዲፕሎማሲ ውጥረት ውስጥ የቆዩት ሁለቱ ጎረቤት ሀገራት ከአንካራው የመሪዎች ስምምነት በኋላ ወደ አዲስአበባ እና ሞቃዲሾ ከፍተኛ ልዑካን ቡድናቸውን ልከው ተወያይተዋል
የፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ የዛሬው ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር እና ያልተፈቱ ጉዳዮችን መፍታት ላይ ያተኮረ መሆኑን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ አመላክቷል፡፡
በዛሬው ዕለት የሀገራቱ መሪዎች የሚያደርጉት ውይይት ውጤት የሶማሊያ እና ኢትዮጵያን የወደፊት ግንኙነት የሚቀርፅ እና ለቀጠናው ሰላም እና ልማት ሰፋ ያለ አንድምታ እንደሚኖረው ተዘግቧል፡፡