በስኮትላንድ ግላስኮው ከተማ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያዊያን ለሜዳሊያ ይጠበቃሉ
የእሁድ ተጠባቂ ውድድሮች ምን ምን ናቸው?
በዛሬው ዕለት ለስፖርት አፍቃሪያን ብዙ ስፖርታዊ ውድድሮች የሚካሄዱበት ዕለት ሲሆን ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ስፖርት አፍቃሪያን ሊዝናኑባቸው የሚችሉባቸው ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡
ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ ከሚካሄዱ የእግር ኳስ ውድድሮች መካከል በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዳማ ከነማ ጋር ምሽት 1 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ፡፡
ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጠባቂው የማንችስተር ደርቢ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን ከዋንጫው የራቀ የሚመስለው ማንችስተር ዩናይትድ በውድድር ዓመቱ እስከ አራተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ሆኖ ለማጠናቀቅ ሲቲን ለማሸነፍ አልያም ነጥብ ለመጋራት እንደሚጫወት ይጠበቃል፡፡
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ማንችስተር ሲቲ ከሊቨርፑል ጋር ያለውን ነጥብ ለማጥበብ እና ዋንጫውን ለማንሳት ጨዋታውን ለማሸነፍ እንደሚጫወት አሰልጣኝ ጋርዲዮላ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ በጣልያን ሴሪኤ ናፖሊ ከጁቬንትስ የሚያደርጉት ጨዋታ ሲሆን ሁለቱም ክለቦች እያሳዩት ያለው ፉክክር ምሽት 4፡ከ45 ላይ የሚደረገውን ጨዋታ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡
በስፔን ላሊጋ ደግሞ የአምናው አሸናፊ ባርሴሎና ከአትሌቲክስ ክለብ ጋር ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታም ከዛሬዎቹ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
የግላስኮው የ 2024 የአለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን ሲያገኝ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ዛሬ በሶስት የፍፃሜ ውድድሮች ላይ ለሜዳሊያ ይጠበቃሉ።
ከእግር ኳስ ውድድሮች ወጣ ስንል ደግሞ በስኮትላንድ ግላስኮው አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው የዓለም ቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ሲሆን በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያዊያን ለሜዳሊያ የሚጠበቁባቸው ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡
ሌሊት ላይ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ በ800 ሜትር የሴቶች ፍጻሜ እንዲሁም በ1500 ሜትር በሁለቱም ጾታዎች የፍጻሜ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ይሳተፋሉ፡፡
የግላስኮው ቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር እስካሁን አሜሪካ በአራት ወርቅ፣ቤልጂየም እና ብሪታንያ እያንዳንዳቸው በሁለት ወርቅ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ድረስ ያለውን ደረጃ ሲያዙ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በአንድ የብር እና አንድ የነሀስ ሜዳልያ በ12ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።