እስራኤላዊው እግር ኳስ ተጨዋች በቱርክ ታሰረ
በፖሊስ የታሰረው ህዝቄል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በእጁ ላይ ባሰረው ፋሻ ላይ የእስራኤል ታጋቾችን የሚደግፍ መልእክት አስተላልፎ ነበር
የቱርክ የፍትህ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የአንታሊያ ዋና አቃቤ ህግ በ28 አመቱ ተጨዋች ላይ ምርመራ እያካሄደ ይገኛል
ሳጊቭ እዝቅኤል የተባለው እስራኤላዊ እግር ኳስ ተጨዋች በቱርክ መታሰሩ ተገለጸ።
አንታሊያስፖር ለተባለው የቱርክ ክለብ የሚጫወተው እግር ኳስ ተጨዋች ሳጊቭ እዝቅኤል "እስራኤል በጋዛ የምታደገውን ጭፍጨፋ" ደግፋል በሚል ምክንያት መታሰሩን ቢቢሲ ዘግቧል።
በፖሊስ የታሰረው እዝቅኤል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በእጁ ላይ ባሰረው ፋሻ ላይ የእስራኤል ታጋቾችን የሚደግፍ መልእክት ማስተላለፉን ተከትሎ በአንታሊያስፖር ታግዶ እንደነበር ዘገባው ጠቅሷል።
ተጨዋቹ በፋሻው ላይ "100 ቀናት፣7/10" በማለት የታገቱት እስራኤላውያን 100 ቀናት እንደሞላቸው መልእክት አስተላለልፏል።
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ሀማስ ያልተጠበቀ እና ከባድ ጥቃት በማድረስ ነበር 1200 ሰዎችን ገድሎ፣ ሌሎች 240 የሚሆኑ ደግሞ አግቶ ወደ ጋዛ የወሰዳቸው።
በህዳር መጨረሻ አካባቢ በኳታር አደራዳሪነት የተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት 100 የሚሆኑ ታጋቾች በሀማስ እጅ እንዳሉ ከስድስት ቀናት በኋላ መጣሱ ይታወሳል።
የቱርክ የፍትህ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የአንታሊያ ዋና አቃቤ ህግ በ28 አመቱ ተጨዋች ላይ ምርመራ እያካሄደ ይገኛል።
አቃቤ ህጉ ተጨዋቹ እንዲታሰር ወይም እንዲለቀቅ የመጨረሻ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሏል።
ተጨዋቹ ማንምም ለመተንኮስ እንዳልፈለገ እና ይልቁንም ጦርነት እንዲቆም መፈለጉን ለፖሊስ መግለጹን የቱርክ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ተጨዋቹ የታሰረው እስራኤል እና ቱርክ በጋዛ የተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ግንኙነታቸው ወደ ዲፕሎማሲያዊ ግጭት ከፍ ባለበት ወቅት ነው።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ጣይፕ ኢርዶጋን እስራኤል በጋዛ የጦር ወንጀል እየፈጸመች ነው፤ በአለምአቀፉ ፍርድ ቤት መከሰስ አለባት ማለታቸው ይታወሳል።