ሞስኮ ወደ ጥቁር ባህር የሚያቀኑ መርከቦች “መሳሪያ ጭነው የሚጓዙ ናቸው” በሚል እንደምትመታቸው ዝታለች
በአለማቀፉ ገበያ የስንዴ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መሆኑ ተገለጸ።
በአውሮፓ በትናንትናው እለት የ8 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ መመዝገቡንና 1 ቶን ስንዴ በ284 ዶላር መገበያየቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
በአሜሪካም የስንዴ ዋጋ የ8 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተዘግቧል።
የዋጋ ጭማሪው ሩሲያ በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን ላይ ጦርነት ካወጀች ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
የስንዴ እና በቆሎ ምርት ዋጋ ጭማሪው የተከሰተው ሩሲያ ከ”ጥቁር ባህር የእህል ስምምነት” መውጣቷን ይፋ ባደረገችና ወደ ጥቁር ባህር የሚያቀኑ የንግድ መርከቦችን እመታለሁ ብላ በዛተች ማግስት ነው።
ባለፉት ሶስት ቀናት ኦዴሳን ጨምሮ የዩክሬን እህል በተከማቹባቸው ወደቦች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናግረዋል።
የዩክሬን የግብርና ሚኒስትር ማይኮላ ሶልስኪም ጥቃቶቹ ከ60 ሺህ ቶን በላይ እህል እንዲወድሙ እና የወደብ መሰረተ ልማቶች እንዲፈራርሱ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
የዋይትሃውስ ቃልአቀባይ አዳም ሆጅ በበኩላችው፥ ሞስኮ በቀጣይም የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝር ነው የገለጹት።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ግን በጥቁር ባህር የሚቀዝፉ ማናቸውም መርከቦች “የጦር መሳሪያ እንደጫኑ ይቆጠራል” ያለ ሲሆን፥ የመርከቦቹ ባለቤት ሀገራትም ዩክሬንን ደግፈው እንደዘመቱ እንወስደዋለን የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያን የእህል ስምምነቱን ላልተገባ አላማ (የጦር መሳሪያ ማዘዋወሪያ) እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ሩሲያ ወደ “ጥቁር ባህር የእህል ስምምነት” የምመለሰው ስንዴ እና ማዳበሪያ እንዳልሸጥ የተጣለው ማዕቀብ ከተነሳላትና እና የሀገሪቱ የግብርና ባንክ ከአለማቀፉ የሽያጭ ስርአት (ስዊፍት) ጋር በድጋሚ ከተሳሰረ ብቻ ነው ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
በመንግስታቱ ድርጅት እና ቱርክ አደራዳሪነት የተደረሰው “የጥቁር ባህር የእህል ስምምነት” የአለም የምግብ ፕሮግራም ከ725 ሺህ ቶን በላይ ስንዴ የዩክሬንን ስንዴ ከወደቦቿ ለማስወጣት አግዟል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ፣ የመን እና አፍጋኒስታንን ጨምሮ አስከፊ የረሃብ አደጋ የተጋረጠባቸው ሀገራትም የኬቭን ስንዴ እንዲያገኙ እድል መፍጠሩ ነው የተወሳው።
የሞስኮን ከዚህ ስምምነት መውጣት ተከትሎም ከዩክሬን ስንዴ የሚያስገቡ ሀገራት ክፉኛ ሊፈተኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።