የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ "የጥቁር ባህር እህል ስምምነት ህጋዊነቱ ዛሬ ያበቃል" ብለዋል
ሩሲያ ከ'ጥቁር ባህር የእህል ስምምነት' ወይም ብላክ ሲ ግሬን ዲል መውጣቷን ክሬሚሊን አስታውቋል።
- በሩሲያ የእህልና የማዳበሪያ ምርት ላይ የሚያጋጥሙ መሰናክሎች ካልተወገዱ የጥቁር ብህር ስምምነት ይቋረጣል አለች
- ሩሲያ አቋርጣው ወደነበረው የጥቁር ባህር ስንዴ ማጓጓዝ ስምምነት ተመለሰች
ባለፈው አመት በቱርክ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) አማካኝነት በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የተዘጋው ኮሪደር ተከፍቶ በዩክሬን ያለው እህል በሰላም ወደ ውጭ እንዲወጣ የሚያስችል ስምምነት ተደርሶ ነበር።
ስምምነቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ቀውስ ለመቀነስ ያለመ ነበር።
ይህ ስምምነት ለበርካታ ወራት የተራዘመ ሲሆን የማብቂያ ጊዜው በዛሬው እለት ነው። ሩሲያ ለበርካታ ወራት ስምምነቱን ለማራዘም ያስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ አልተሟላም የሚል ቅሬታ ስታሰማ መቆየቷ ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት ሩሲያ ከስምምነቱ ወጥታለች።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ "የጥቁር ባህር እህል ስምምነት ህጋዊነቱ ዛሬ ያበቃል" ብለዋል።
ቃል አቀባዩ " እንዳለመታደል ሆኖ ሩሲያን የሚመለከተው የስምምነቶቹ ክፍል እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፤ ስለዚህ የስምምነቱ ገዥነት ተቋርጧል።" ሲሉም ተናግረዋል።
ሩሲያ እህል እና ማዳበሪያ ወደ ውጭ ለመላክ ያሉባት እንቅፋቶች መፍትሄ እንዲያገኙ ለረጅም ጊዜ ስትጠይቅ ቆይታለች።
የሩሲያ እና ዩክሬን አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን በዛሬው እለት የክሪሚያ ድልድይ በዩክሬን ተመትቷል የሚል ክስ ሩሲያ አቅርባለች።